ለቆዳ፣ ኬሚካል እና ለተለያዩ ፋብሪካዎች በቂ የጨው ግብዓት ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው-የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለቆዳ፣ ኬሚካል እና ለተለያዩ ፋብሪካዎች በቂ የጨው ግብዓት ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው-የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2016 (ኢዜአ)፦ ለቆዳ፣ ኬሚካል፣ እና ለሌሎች ፋብሪካዎች በቂ የጨው ግብዓት ለማቅረብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት ለኢንዱስትሪዎች ከሚፈልጉት ጨው ውስጥ እየቀረበ ያለው ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ምቹ አሰራሮች እየተዘረጉ መሆኑ ተጠቁሟል።
ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የጨው አቅርቦት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ ለችግሮች ዕልባት ለመስጠት የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያስተባበር ኮሚቴ ተቋቁሟል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሀሰን መሀመድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ጨውን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በየዓመቱ ከ26 ሚሊዮን 353 ሺህ በላይ ኩንታል ጨው ይፈልጋሉ።
ነገር ግን እየቀረበ ያለው 50 በመቶ ብቻ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም አገሪቱ ካላት የጨው ሀብት ጋር ሲነጻጸር እየቀረበ ያለው በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም ይላሉ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የወጡ አሰራሮች በአግባቡ አለመተግበራቸው፣ በጨው ፈላጊዎች እና አቅራቢዎች መካከል ያለው ትስስር አለመጠናከር፣ የጨው አቅራቢዎች ቁጥር ውስን መሆን እንዲሁም ህገ ወጥ ደላሎች ለግብዓት እጥረቱ ተጠቃሽ መንስኤዎች ናቸው።
በዚህ የተነሳም በጨው ግብዓት የሚሰሩ ኢንዱስትሪዎች እንዳይስፋፉ፣ የሚፈለገው የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ውጭ ምንዛሬ እንዳይገኝ ማድረጉንና ከውጭ የሚገባ ምርትን የመተካት ጥረት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት ምቹ አሰራሮችን እየዘረጋ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመጠቀም በዘርፉ ያሉ የፋይናንስ፣ የአሰራር እና አቅርቦት ችግሮች እንዲፈቱ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
የጨው አምራች ማህበራትን አቅም ማጎልበት ሌላው የመፍትሄ አቅጣጫ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ሁለት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጨው አቅርቦት ላይ እንዲሰማሩ የአፋር ክልል ምክር ቤት መወሰኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የልማት ድርጅቶችን በማጠናከር ወደ ሥራ ማስገባት ሌላው የትኩረት መስክ ነው ብለዋል።
በኢንዱስትሪ ጨው አቅርቦት ሰንሰለቱ ዙሪያ ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ በማጠናከር ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማምጣት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የአፋር ክልል ንግድ፣ ገበያ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ሁመድ በበኩላቸው በክልሉ የአገር ውስጥ ፍጆታን በሚፈለገው ደረጃ መመለስ የሚችል የጨው ኃብት መኖሩን ተናግረዋል።
ጨው አምራቾች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመጠቀማቸው በሚፈለገው ደረጃ እንዳያመርቱ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ምርት የሚያቀርቡበት ዋጋ ወቅቱን ያገናዘበ አለመሆኑ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የጨው ምርቶችን አሽጎ በማቅረብ ላይ የተሰማራው ወጣት ሄኖክ ገብረመድህን በሰጠው አስተያየት በቂ የጨው ምርት ከማቅረብ ባሻገር ለጥራቱ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመልክቷል።