ቀጥታ፡

አዲስ አበባ በቀጣይ ቀናት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መድረኮችን ታስተናግዳለች -  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2016 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ በቀጣይ ቀናት  ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መድረኮችን እንደምታስተናግድ የከተማ አስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ እናት ዓለም መለሰ በሰጡት መግለጫ መስከረም 28 እና 29/2016 የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የልህቀት ማዕከልን ለማቋቋም ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በውይይቱ የልህቀት ማዕከሉ ስትራቴጂካዊ እቅድና ትልሞች ላይ ምክክር እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የተለያዩ አገራት የዘርፉ ምሁራን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኃላፊዎች፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል። 

በመዲናዋ የተተገበረው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ከጅምሩ ያስገኘው ስኬት አገራዊና አህጉራዊ ተሞክሮ ለመሆን በቅቷል ነው ያሉት ኃላፊዋ።

በሌላ በኩል ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ እና የአፍሪካ ከንቲባዎች የእርስ በርስ መማማሪያ መድረክ ይከናወናል ብለዋል።

በሁነቱ ላይ የአፍሪካ አገራት የተለያዩ ከተሞች እንዲሁም የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች፣ የተለያዩ አገራት ተወካዮችና ሌሎች እንግዶች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 1/2016 በሚካሄደው የአገር አቀፍ መሪዎች የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የውጭ አገራት ተሳታፊዎች እንደሚገኙበትም አመልክተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በቆይታቸው በከተማዋ የሚገኙ ፓርኮችና የልማት ስራዎችን እንደሚጎበኙ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም