ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የእህል ድጋፍ አደረገ

ደብረ ብርሀን ፤መስከረም 23 / 2016 (ኢዜአ)፡-  የኢትዮጰያ ቀይ መስቀል ማህበር  በደብረ ብርሃን ከተማ በጊዜያዊ  መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው እንዳሉት፤ በከተማው ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ችግር ለማቃለል  ማህበሩ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

ዛሬ ደግሞ ለአንድ ሺህ ሃምሳ ሰዎች የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ከተደረገው ድጋፍ ውስጥም 50 ኩንታል የጤፍ ዱቄት፣ 113 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 15 ኩንታል ሽሮና 1 ሺህ 335 ሊትር የምግብ ዘይት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።


 

የወይንሸት መጠለያ ካምፕ የተፈናቃዮች ተወካይ አቶ ቤትየ ደርቤ በሰጡት አስተያየት፤ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍም ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚያግዛቸው ጠቅሰው፤ በቀጣይም እገዛ እንደሚያሻቸው ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ይቀርብ የነበረው ድጋፍ በመቀነሱ በካምፕ ውስጥ ሆነው ከቤተሰቦቻቸውጋር ተቸግረው መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ የሺህ ነገሰ ናቸው።

ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍም ወቅታዊ ችግራቸውን የሚቃልል መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ መሰል ድጋፍ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም