ተቋማት አረጋውያንን በመደገፍና በመንከባከብ የሚጠበቅባቸውን ማኅበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው - የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማት አረጋውያንን በመደገፍና በመንከባከብ የሚጠበቅባቸውን ማኅበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው - የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2016 (ኢዜአ)፦ተቋማት አረጋውያንን በመደገፍና በመንከባከብ የሚጠበቅባቸውን ማኅበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።
ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን "የአረጋውያንን መብት ማክበር ትውልድን ለማሻገር" በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም ለ33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡
በመርሃ ግብሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋውያን ተሳትፎ፣ ድጋፍና እንክብካቤ ማስተባበሪያ ሃላፊ አቶ ይትባረክ አበበ እንዳሉት፣ አረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ ከተደረገላቸው በትውልድ ግንባታና ልማት ላይ ያላቸው ተሳትፎ ከፍ ይላል፡፡
መንግስት አረጋውያን በትውልድ ግንባታ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል ህግ አውጥቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ መንግስት የአረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን ቤት ማደስ፣ ማዕድ ማጋራትና መሰል ተግባራትን በማከናውን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቀጣይም አረጋውያን ያላቸውን እምቅ አቅም ለትውልድ ቀረፃ ማዋል እንዲችሉ የመንግስት ተቋማት አረጋውያን በአግባቡ መንከባከብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በዚህ ረገድ ሁሉም የመንግስት መዋቅሮች ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንዲችሉ ሚኒስቴሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ጌታቸው ክፍሉ ለአረጋውያን በቂ ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
እነዚህ ትላንትን ያሻገሩ ነገን የሚገነቡ ትውልዶችን የሚቀርጹ የሀገር ባለውለታዎች በቂ ህክምና፣ መጠለያ፣ ምግብና አልባሳት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
መንግስት የአረጋውያንን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡