የዳውሮ ታርጫ የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካ ግንባታ የፊታችን ጥቅምት ወር ይጠናቀቃል- የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2016 (ኢዜአ)፦በዳውሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ ወረዳ በግንባታ ላይ የሚገኘው የታርጫ ድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካ ግንባታ የፊታችን ጥቅምት ወር እንደሚጠናቀቅ የፋብሪካው ባለቤት የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር ገለፀ።

የማዕድን ሚኒስቴር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ የታጠበ የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ ለመተካት በ2014 ዓ.ም በተመረጡ ቦታዎች ለስምንት ሀገር በቀል ኩባንያዎች ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።

ከእነዚህም መካከል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ ወረዳ የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር የተሰኘው ኩባንያ የሚያስገነባው የድንጋይ ከሰል ማበልፀጊያ ፋብሪካ አንዱ ነው።

የኢቲ ማዕድን ልማት ተወካይ ወንድሙ ምትኩ እንዳሉት፤ በ2014 ዓ.ም የስራ ፈቃድ ያገኘው ፋብሪካው አሁናዊ የሲቪል ግንባታ አፈጻጸሙ 85 በመቶ ተጠናቋል።

ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የግንባታ ግብዓቶችን እየተጠቀመ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ሳምንታት ማሽን መትከልን ጨምሮ ቀሪ ስራዎችን በማጠናቀቅ በጥቅምት ወር ውስጥ አጠናቆ ለማስመረቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለፋብሪካው አጠቃላይ ግብዓት ግዥና ግንባታ ስራዎች እስካሁን 4 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰው፣ አጠቃላይ ግንባታው 5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እንደሚፈጅም ገልጸዋል።

ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ስራ ሲገባ ለሲሚንቶ፣ ለብረት፣ የወረቀት፣ ለሴራሚክ፣ ለጂፕሰም እና ሌሎች ፋብሪካዎች ግብዓትነት የሚውል የታጠበ የድንጋይ ከሰል እንደሚያቀርብ ጠቅሰዋል።

በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምርም በሰዓት 150 ቶን፣ በዓመት ደግሞ አንድ ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል የማጠብና የማበልጸግ አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ይህም ሀገሪቷ በከፍተኛ ወጪ የምታስገባውን የውጭ ምንዛሬ በመቀነስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ድርጅቱ በዳውሮ አካባቢ ለ20 ዓመታት ፈቃድ የወሰደበት የድንጋይ ከሰል ክምችት በቂ ባለመሆኑ በኮንታ እና ጋሞ ዞኖች የድንጋይ ከሰል ክምችትን ለመጠቀም የአዋጭነት ጥናት ማድረጉን ተናግረዋል።

የትምህርትና የጤና ተቋማት ግንባታዎችን ጨምሮ ማህበራዊ ኅላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸው፤ በፋብሪካው ግንባታ ለ410 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደፈጠረ አንስተዋል።

ፋብሪካው በአካባቢው ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ እንዳይኖረው ዘመናዊ የተረፈ ምርት መልሶ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ የሚገጠምለት ስለመሆኑም አረጋግጠዋል።

አያይዘውም በአካባቢው ያለውን የማዕድን ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል መንግስት የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማፋጠን አለበት ብለዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ደምሴ በበኩላቸው፤ ዞኑ ድንጋይ ከሰልን ጨምሮ በርካታ ማዕድናት እንዳሉት ጠቅሰው፤ እስካሁን በድንጋይ ከሰል ማምረት ስድስት ባለሃብቶች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።


 

የድንጋይ ከሰል በተለያዩ ወረዳዎች በስፋት መኖሩን ገልፀው፣ ይህም ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።

በድንጋይ ከሰል ማዕድን ኢንቨስመንት በስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ዕምርታ መገኘቱን ጠቁመው፣ ሌሎች ባለሃብቶች በወርቅ፣ ብረት፣ የኖራ እና ሌሎች ማዕድናት ዘርፍም እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢቲ ማዕድን ልማት ያቋቋመው የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው የሚያስገኘው ሁለንተናዊ ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የዳውሮ ዞን ዕምቅ የማዕድን፣ የቱሪዝምና የግብርና ሀብትን ለሀገር እድገት ለማዋል የፌደራል መንግስት የመንገድና የመብራት መሰረተ ልማትን የማሟላት ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም