የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ወደ ስራ መግባታቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ወደ ስራ መግባታቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2016 (ኢዜአ)፦ በልዩ ድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሰላም እንዲከበር መላው የፀጥታ አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
ግብረ ሀይሉ የአዲስ አመት፣ የመስቀልና የመውሊድ በዓላት አከባበርን በመገምገም በቀጣይ ቀናት የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል።
የፀጥታ አካላት አመራሮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸውን ጥምረት አጠናክረው በጋራ በመስራታቸው በያዝነው አዲስ አመት የተከበሩ ልዩ ልዩ በዓላትን በሰላምና በስኬት ማክበር እንደተቻለ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ አስታውሰዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ክለውም ህዝብ የሚታደምባቸው የኢሬቻ ሆራ ፊንፍኔ እና በቢሾፍቱ የሚከበረው የኢሬቻ ሆራ አርሲዲ በዓላት ባህላዊ ስርዓታቸውን ጠብቀው እንዲከበር ግብረ ኃይሉ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደስራ መግባቱን ተናግረዋል።
በሁለቱም ከተሞች የሚከበሩት የኢሬቻ በዓላት የፀጥታ ስራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚከናወን መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላት በሰላምና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ስር ተቀናጅተው በመስራታቸው ውጤታማ ስራ መስራት እየተቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢሬቻ በዓል ድባብ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ለማሳደር የሚደረጉ ማንኛውም ህገወጥ ተግባራት በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል ብለዋል።
የፀጥታ አካላትም ይህን የማይታገሱ መሆኑን አስረድተው የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ልዩ የህዝብ አደረጃጀቶችን በፀጥታ ሰራ ላይ እያሳተፈ እንደሆና ይሄው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
በያዝነው ዓመት በርካታ ህዝብ የታደመባቸው ልዩ ልዩ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሥኬታማ ስራ ማከናወኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተናግረዋል።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር የበዓሉ ታዳሚዎች እና ህብረተሰቡ የተለመደውን ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በበዓሉ አከባር ላይ ከባህላዊ አከባበሩ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራት፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ጽሁፎችና መልዕክቶችን ይዞ መገኘት እንዲሁም ባህላዊ ሥርዓቱን ሊያውክ የሚችል ተግባር ማከናወን ተቀባይነት የሌለውና ፍፁም ክልክል መሆኑን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።
ህብረተሰቡ ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲያጋጥሙት በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ግብረ ኃይሉ ጥሪ አስተላልፏል።