ተቋማት የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ በአግባቡ እንዲያስወግዱ የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት እየተሰራ ነው - አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23/2016(ኢዜአ)፦ የመንግሥትና የግል ተቋማት የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ በአግባቡ እንዲያስወግዱ የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ። 

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ ክምችት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። 

ለአብነትም ከሦስት ዓመታት በፊት የተካሄደ ጥናትም በኢትዮጵያ 43 ሺህ ቶን የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ ክምችት መኖሩን አመላክቷል።

በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት ዳይሬክተር ጄኔራል ግርማ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከኤሌክትሪክና ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የቆሻሻ ክምችቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።


 

በተለይም የመንግሥት ተቋማት የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻን በማከማቸት በኩል ተቀዳሚ ተጠቃሽ መሆናቸውንም በመጠቆም። 

በመንግሥት ግዥ አገልግሎት የንብረት ማስወገድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሹንቃ አዱኛ፤ በተመሳሳይ  የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻን ክምችት ጨምሯል ብለዋል።  


 

ለዚህም የመንግሥት ተቋማት የማይጠቀሙባቸው የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ዕቃዎችን እንዲወገዱ የሚያወጡት የጨረታ መነሻ ዋጋ ከፍተኛ መሆን በምክንያትነት አንስተዋል።  

እነዚህን የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ ክምችት በአካባቢ ላይ የሚያደርሱትን አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት ተቋማት በአግባቡ እንዲያስወግዱ ጥሪ አቅርበዋል። 

የመንግሥትና የግል ተቋማት የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ መሳሪያ በድጋሚ መጠቀምን፣ ማደስንና መልሶ ጥቅም ላይ የማዋልን ዝንባሌያቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል። 

ባለሥልጣኑ በተያዘው ዓመት ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ ለአምራቹ እንዲመለሱ ማድረግ የሚያስችለውን የተራዘመ የአምራችነት ሥርዓት ምዝገባን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።  

ይህም አስመጪዎች ከአምራቾች ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጥሩና የሚያስመጡትም ዕቃ ጥራት ያለው እንዲሆን ከማገዝ ባለፈ የቆሻሻ አስተዳደሩ ሥርዓቱን የተሳለጠ ያደርጋል ነው ያሉት። 

እንደ አቶ ሹንቃ ገለጻ፣ ቀደም ሲል የመንግሥት ተቋማት የማይገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ወደ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በማምጣት ሲያስወግዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 


 

ይሁንና ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ይህ አሠራር ቀርቶ ተቋማት በራሳቸው ንብረቶቹን እንዲያስወግዱ መመሪያ መሰጠቱን ገልፀዋል። 

ይሁንና ተቋማቱ የማይገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች እንዲያሳውቁ በማድረግ ንብረቶቹ በፍጥነትና በአግባቡ የሚወገዱበት መንገድ ለማመቻቸት ተቋማቸው እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ደንብ 425/2011 ላይ በግልፅ እንደተመላከተው  የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ፣ ከጨረር  አመንጪ መሳሪያዎች ውጭ ሁሉም ዓይነት የተጣለ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ እና የመሳሪያ  ክፍል የሚያጠቃልል ነው።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም