ቀጥታ፡

በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ጣቢያዎች ግንባታ ይጠናቀቃሉ - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23/2016(ኢዜአ)፦በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት ስምንት የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ጣቢያዎች ግንባታ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ። 

የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ኃይል ማመንጨት፣ የመነጨውን ኃይል ማስተላለፍና በጅምላ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ሥራዎችን ያከናውናል።

ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት ከተለያዩ የኃይል አማራጮች በተገነቡ የኃይል ማመንጫዎች 5 ሺህ 200 ሜጋዋት ኃይል ማመንጨት እንደተቻለ ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመትም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተጨማሪ ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት ስለሚጀምሩ የአገሪቱ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይበልጥ እንደሚያድግ ገልፀዋል።  

ተቋሙ ከያዛቸው 17 የማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ውስጥ ስምንቱን በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች፤ የደጀን ደብረማርቆስ አሸጎዳ ደሴ ሆርማት፣ ቡታጅራ ወራቤ፣ የአዘዞ ጭልጋ መቱ ማሻ፣ የአዋሽ ወልዲያ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር፣ የባህርዳር ወልዲያ ኮምቦልቻ ፕሮጀክት ውስጥ ከባህርዳር እስከ ወልዲያ ያለው እንዲሁም የጫካ ፕሮጀክት እንደሆኑም አመላክተዋል። 


 

ከዚህ በተጨማሪ በአዳማ ሁለት እንዲሁም በኮተቤ በሚገኘው የተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ውስጥ ያሉት ሁለት ፕሮጀክቶች ይገኛሉ ብለዋል።  

የበቆጂና ደብረታቦር ማከፋፈያ ጣቢያ፣ የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንዲሁም የመቀሌ ዳሎል የማስተላለፊያና ሰብስቴሽን ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።  

በአራት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል ማስተላለፊያ መስመር፣  የኢትዮ ጅቡቲ ሁለተኛ ሰርኪዩትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥልጠናና የልህቀት ማዕከል ግንባታ በተያዘው ዓመት እንደሚጀመሩም ጠቅሰዋል።

ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉ ፕሮጀክቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።  

 

    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም