የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ውጤት ያገኘባቸውን ሁለት የስኳር ድንች ዝርያዎች ይፋ አደረገ

ጂንካ ፤ መስከረም 23/2016 (ኢዜአ)፡-የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር  ውጤት ያገኘባቸውን  'ካቦዴ'' እና ''በርኩሜ'' የተሰኙ ሁለት የስኳር ድንች ዝርያዎችን ይፋ አደረገ።

በማዕከሉ ጥናትና ምርምር ውጤታማነታቸው የተረጋገጠው ሁለት የስኳር ድንች ዝርያዎች አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም ከሚጠቀሙት ዝርያ ጋር ሲነፃፀር ከሁለት እስከ ሶስት እጥፍ ምርት መስጠት እንደሚችሉም ማዕከሉ አስታውቋል ።

የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል አግሮኖሚ ተመራማሪ አቶ አወቀ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት የምርምር ማዕከሉ በአካባቢው ያለውን የስኳር ድንች ዝርያ በማሻሻል ምርታማነቱን በእጥፍ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

ማዕከሉ ከሀዋሳ የግብርና ምርምር ማዕከል ያመጣቸውን ''ካቦዴ'' እና ''በርኩሜ'' የሚል ሳይንሳዊ መጠሪያ ያላቸውን የስኳር ድንች ዝርያዎች በሳይንሳዊ ጥናት በማስደገፍ ከአካባቢው ሥነ-ምህዳር ጋር የማላመድ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

'ካቦዴ'' ብርቱካናማ ቀለም ያለው ሲሆን ''በርኩሜ ''ደግሞ ነጭ ቀለም ያለው የስኳር ድንች ዝርያ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በምርምር ማዕከሉ የተሰራው ጥናት እንዳረጋገጠው ''ካቦዴ''የተሰኘው የስኳር ድንች ዝርያ በአንድ ሄክታር እስከ 600 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ ገልፀው ''በርኩሜ ደግሞ በሄክታር እስከ 920 ኩንታል ምርት ይሰጣል" ብለዋል ።

''ካቦዴ''የተሰኘው ብርቱካናማ የስኳር ድንች ዝርያ ከ''በርኩሜ''ጋር ሲነፃፀር ምርት አሰጣጡ ያነሰ ቢሆንም በውስጡ ያለው  የቫይታሚን ይዘቱ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል ።

እነዚህ ሁለት የስኳር ድንች ዝርያዎች የአፈር ለምነትን ከመጨመር ባለፈ የአካባቢውን የአየር ሁኔታ በቀላሉ በመላምድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡ መሆናቸው ተገልጿል።

በአካባቢው አርሶ አደሮች እየተጠቀሙበት የሚገኘው የስኳር ድንች ዝርያ በሄክታር እስከ 300 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ የጠቀሱት ተመራማሪው፥ ማዕከሉ በምርምር ያገኛቸው ዝርያዎች ግን ከተጠቀሰው በሁለት እና ሶስት እጥፍ የበለጠ ምርት መስጠት እንደሚችሉ ተናግረዋል ።

በአርሶ አደሮች እጅ ያለው የስኳር ድንች ዝርያ ምርት ለመስጠት ከ6 እስከ 7 ወራት እንደሚወስድበት ተመራማሪው ገልፀው በምርምር የተገኙት የስኳር ድንች ዝርያዎች ግን ከ4 እስከ 5 ወራት ውስጥ ምርት እንደሚሰጡም አረጋግጠዋል ።


 

በምርምር የተገኙት የስኳር ድንች ዝርያዎች በአካባቢው አሁን ካለው የስኳር ድንች ዝርያ ጋር ሲነፃፀሩ ድርቅና በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ተመራጭ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ተክሌ ዮሴፍ በበኩላቸው በምርምር የተገኙት የስኳር ድንች ዝርያዎች የምግብ ዋስትናን በማረጋገጡ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

በቀጣይም የማዕከሉ የምርምር ግኝት የሆኑትን የስኳር ድንች ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች የማሰራጨትና ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል ።


 

የአካባቢው አርሶ አደር አቶ ማሞ አቅና፥ ከዚህ ቀደም ለበርካታ አመታት  ስኳር ድንች የማልማት ልምድ  እንደነበራቸው ገልፀው ከአካባቢው ዝርያ በሄክታር ከ200 እስከ 300 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል ።

ይህ በሙከራ ደረጃ የለማው ስኳር ድንች ድርቅና በሽታን በመቋቋም እጥፍ ምርት መስጠቱ ይበልጥ ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል።

በቀጣይም ከምርምር ማዕከሉ በሚያገኙት የዘር ድጋፍ በማሳቸው የተሻሻሉ ዝርያዎችን በስፋት በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን ማቀዳቸውንም ገልጸዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም