"በገበታ ለትውልድ" የሚለማው የደንቢ ሀይቅ

"በገበታ ለትውልድ" ስለሚለማው የደንቢ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ምን ያህል ያውቃሉ?

(በቀደሰ ተክሌ ከሚዛን አማን)

ደንቢ ሃይቅ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ሲሆን በእኛ የዘመን ቀመር በ1970ዎቹ የተሠራ ነው። በተፈጥሮ መስህቦች የተከበበው የደንቢ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ለአካባቢው ብርሃንን ይፈነጥቅ ዘንድ የተሰራውን የቀድሞ የደንቢ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብን ተከትሎ የተፈጠረ ሃይቅ ነው።

የደንቢ ሃይቅ ለአካባቢው ማህበረሰብ ባለውለታ ነው፤ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ብርሃን ያገኙበት ነውና። ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቡ ከመልክዓ ምድሩ ጋር እንዲስማማ ተደርጎ የተገነባ በመሆኑ ውሃው ከላይ ወደ ታች በሁለት ምዕራፍ ቁልቁል እንዲወረወር ዕድልን ፈጥሮለታል። የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ሃይልን ለማመንጨት በዝግታ የሚወርደው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሃይል አመንጭቶ ሲወጣ እጅግ ውብ የሆነ ፏፏቴን  ፈጥሮ ወደ ታች የሚወርደው ነው።

የደንቢ ፏፏቴ ከሃይቁ ወረድ ብሎ ስለሚገኝ "ደንቢ ሃይቅና ፏፏቴ" እየተባለ ይጠራል። ሃይቁን አይቶ ፏፏቴውን ሳያዩ መመለስ የማይቻል ነገር ነው። የደንቢ ፏፏቴ ከላይ ከዓለት ዓለት እየተጋጨ ሲወረወር የሚያሰማውን በግርማ ሞገስ በታጀበ ድምጽ፤ በተራራ ቀበቶ ተገምዶ ወደ ማረፊያ ቦታው ሲምዘገዘግ በለመለመው መስክ ላይ አሻግረው የሚቃኙት የተፈጥሮ ውበት ነው። ያሻው ወደ ተራራው ጫፍ ጠጋ ብሎ እንደ ጢስ በሚተነው የውሃ አካል ፊቱን እያስመታ አልያም  ከሃይቁ ፊት ለፊት ራቅ ብሎ ተቀምጠው እየተመለከቱ መንፈስን የሚያድሱበት ውብ የፏፏቴ ሥፍራ ነው።


 

ከላይኛው የግድቡ አናት ወደ ታችኛው ለመውረድ 640 ደረጃዎችን አቆልቁሎ መጓዝን ይጠይቃል። ይህ ትዕይንት ደግሞ  የደንቢ ሃይቅ ሌላኛው መስህብ ነው። የደረጃዎቹን የመውጣትና የመውረድን ድካም አረንጓዴ ካባ የደረበው የሥፍራው ልምላሜ እንዲዘነጋ ያደርጋል። የደንቢ ሃይቅ አካባቢ ቀልብን ስቦ ድካምና ሌላ ሃሳብን አስትቶ ሃሴትን የሚያጎናጽፍ የተፈጥሮ ፀጋን የታደለ ነው። 

የደንቢ ሃይቅና ፏፏቴ ግርማ ሞገስ ምስጢሩ የአካባቢው ደን ነው። በረጃጅም እድሜ ጠገብ የሃገር በቀል ዛፎች የተከበበ ነው። በእምቅ ደኑ ውስጥ የሚገኙ አዕዋፋት ለሚገባ ለሚወጣው ሁሉ እንደየ ፀጋቸው ያዜማሉ። ጉሬዛዎችና ጦጣዎች ከዛፍ ወደ ዛፍ እየዘለሉ እጅ ይነሳሉ። ይህ አካባቢ የተጎናጸፈው የቱሪዝም ፀጋ ከብዙዎች ዐይን ርቆ ቆይቷል። አሁን ግን በቃ ብሎ ሚሊዮኖች ሊጎበኙት ጊዜው ተቃርቧል። አካባቢው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምሥረታን ተከትሎ ወደ ሥፍራው ጎራ ለሚሉ ሚኒስትሮችና የሃገር መሪዎች የማስተዋወቅ ሥራ በመሠራቱ "የገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክት አንዱ አካል ሊሆን ችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ቦታው ድረስ በመሄድ፣ በማየትና ለዓለም ጭምር በማስተዋወቅ የደንቢ ሎጅ ግንባታን የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። በመድረኩ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሚለማው የደንቢ ሃይቅ ሎጅ ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ተኩል የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው። በተጨማሪም በደንቢ ሃይቅ ሎጅ አቅራቢያም ሌላው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የአየር ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ይበልጥ አካባቢውን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ነው። የሎጅ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ፤ ደንቢ ላይ ያረፈ ጎብኚ ከ40 በላይ የሚፍለቀለቁ የዑሲቃ ፍል ውሃ ቦታዎችን፣ የጋርንናንሳ ተራራን እና ሌሎች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቤንች ሸኮ ዞን የተፈጥሮ ፀጋዎችን በቅርብ ርቀት መጎብኘት ይችላል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ በርካታ የቱሪዝም ሃብቶችን በዙሪያው አቅፎ የያዘው ደንቢ በቅርቡ የቱሪዝም ኢኮኖሚ አነቃቂ ሃይል ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በነደፉት የ"ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክት ሲለማ ከሃገር ውስጥ ባሻገር ከሃገር ውጭ በርካታ ጎብኚዎችን በማስተናገድ የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት ፕሮጀክት መሆኑንም ሳይዘነጉ። እንደዚህ አይነት ሃገራዊ ፕሮጀክቶች በአካባቢያቸው የተለመዱ አለመሆናቸውን ጠቅሰው የመንግስትን እይታና በአካባቢው ያለውን ሃገራዊ አቅም ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም አድንቀዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ መስህብ ሃብቶች እንዳሉት ገልጸው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለውን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለመቀላቀል መንግስት የከፈተውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባ ነው የጠቆሙት። ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት መሠረት ተቀምጦለት እየተገነባ ያለውን የሚዛን አማን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታን መልካም አጋጣሚውን ለመጠቀም አንዱ ዕድል እንደሆነም ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶችን ቆይታ ለማራዘም እና ወደውት ተደስተው እንዲመለሱ ለማስቻል ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እናደርጋለን ያሉ ሲሆን በቅርብ ርቀት ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ምቹ የማድረግ ሥራም በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው አቶ ያሬድ ካንጃ ደንቢ በቅርብ ርቀት ቢገኝም ያልለማ በመሆኑ ብዙዎች የመጎብኘት ዕድል እንዳላገኙ ተናግረዋል። ደንቢ ሃይቅ እና ፏፏቴ ከሃይቅነትና የቱሪስት መስህብነት ባሻገር በሥራ ዕድል ፈጠራም ጭምር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው ነው ያሉት። የሎጁ መገንባት የዞኑን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ወደ ዓለም ገበያ ያስገባል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውንም አቶ ያሬድ አልሸሸጉንም። "እንደ አካባቢው እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አቅም አንጻር ይህ ጅምር ነው፤ በቀጣይ በርካታ ፕሮጀክቶችን እንጠብቃለን" ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም