አገራት በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች ነው - አቶ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
አገራት በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች ነው - አቶ አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አገራት በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራች መሆኗን የኢኒሼቲቩ ሊቀመንበርና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ኢኒሼቲቩ 18ኛ የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብሰባውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በስብሰባው የኢኒሼቲቩ ሊቀመንበርና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ጨምሮ የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ የትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኢኒሼቲቩ አባል አገራት ሚኒስትሮችና የልማት አጋሮች ተወካዮች ታድመዋል።
ውይይቱ በአፍሪካ ቀንድ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን ልማት ማጠናከር ዓላማ ያደረገውና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2024 እስከ 2028 የሚተገበረው ፍኖተ-ካርታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
በፍኖተ-ካርታው አማካኝነት የሚከናወኑ ተግባራት አስቸኳይ፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ በሚል ተከፋፍሎ እንደሚተገበር ተመላክቷል።
በውይይቱ የድንበርና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የተመለከቱ ፍኖተ-ካርታዎች ተግባራዊነትና በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን የአፈጻጸም ሂደት ግምገማ እንደተደረገበት የኢኒሼቲቩ ሊቀመንበርና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገልፀዋል።
የፕሮጀክቶቹ ትግበራ እንዲፋጠን በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የኢኒሼቲቩ ሊቀመንበር የሆነችው ኢትዮጵያ አገራትን በአባልነትና በታዛቢነት እንዲሳተፉ ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ነው ብለዋል።
በዚህም ኢኒሼቲቩን ለመቀላቀል ያለው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፤ ዩናይትድ ኪንግደምና ፈረንሳይ በስብሰባው ላይ በታዛቢነት መገኘታቸው የዚሁ ማሳያ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
ኢትዮጵያ በአባል አገራቱ መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸው፤ በ2024 የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የመሪዎች ጉባዔ ለማዘጋጀት ሃሳብ ማቅረቧን ጠቁመዋል።
የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን እንዳሉት ሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች የልማት ፍኖተ-ካርታ ትግበራን እንደምትደግፍ አመልክተዋል።
በፍኖተ-ካርታው ትግበራ በአዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ዜጎች የቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመሠረተ-ልማት የማስተሳሰር ጉዳይ ትኩረት እንደሚሻ ገልፀዋል።
ሕብረቱ የጅቡቲ ኮሪደርን በማልማት የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በቻድ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ ተፈናቃዮችንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለመደገፍ 30 ሚሊየን ዩሮ ክልላዊ ምላሽ ፕሮግራም መዘጋጀቱን ነው ኮሚሽነሯ የጠቆሙት።
በአፍሪካ ቀንድ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ፣ ግንኙነትን ማሻሻልና የድንበር ተሻጋሪ ንግድን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ፍኖተ-ካርታው የባለብዙ ወገኖችን ተሳትፎ የሚያሳይና የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች ልማትን ለማፋጠን እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
"የድንበር አካባቢዎችን ማልማት ለአንድ አካል የሚተው ጉዳይ አይደለም" ያሉት ዋና ፀሐፊው ልማቱ ለአገራት ሰላም፣ መረጋጋት፣ ብልጽግና፣ ለቀጣናው እድገትና አልፎም ለተቀረው ዓለም ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ለፍኖተ-ካርታው ትግበራ ስኬታማነት በአጋርነትና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) የተቋቋመ ኢኒሼቲቭ ነው።
ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ኤርትራ የኢኒሼቲቩ አባል አገራት ናቸው።