የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ያደረገው ድጋፍ ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለሱን ያሳያል - አቶ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ያደረገው ድጋፍ ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለሱን ያሳያል - አቶ አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ያደረገው ድጋፍ ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ወደነበረበት መመለሱን የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
አውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚተገበር የ650 ሚሊየን ዮሮ ዓመታዊ የባለብዙ ዘርፍ የድጋፍ መርኃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ አደርጓል።
የድጋፍ ማዕቀፉን የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ጋር ፈርመዋል።
መርኃ ግብሩ ላይ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት አምባሳደሮች ታድመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት፣ ድጋፉ በኢትዮጵያ መንግሥት በሚተገበሩ ዋና ዋና የልማት ፕሮግራሞች ፋይናንስ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
ድጋፉ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በተወሰነ ደረጃ ተቀዛቅዞ የቆየውን የልማት ፋይናንስ ትብብር ወደ ነበረበት መመለሱን ያሳያል ነው ያሉት።
ድጋፉ በአውሮፓ ኅብረትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ያለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉን አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ የሰላም ግንባታዋን በማጠናከር ከልማት አጋሮች ጋር ያላትን የትብብር ማዕቀፍ እየተጠናከረ የሚሄድ መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ድጋፉ በኢትዮጵያ ከተደረሰው የሠላም ሥምምነት ማግስት ይፋ መደረጉ የአውሮፖ ኅብረት ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳየበት መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረትና አባል ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስና በኢትዮጵያ የጸና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ቁርጠኛ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።
ድጋፉ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለሰው ኃይል ልማት፣ ለመልካም አስተዳደርና ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም እምነታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ድጋፉ ለአረንጓዴ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ፣ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ታዳሽ ኃይል ልማት፣ ለመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚውል ይሆናል ነው ያሉት።
ኮሚሺነር ጁታ በዛሬ ውሏቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ጋር መምከራቸው ታውቋል።
ኮሚሺነር ጁታ ኡርፒላይነን በኢትዮጵያ ይፉዊ የሥራ ጉብኝ ለማድረግ ትላንት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።