ኢትዮጵያ አስተማማኝና ፍትሕዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አስተማማኝና ፍትሕዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አስተማማኝና ፍትሕዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የዓለም አቀፍ ቴሌኮም ኅብረት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
በሕብረቱ አህጉራዊ ጉባኤ ላይ የአፍሪካን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠንና ዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።
በዓለም አቀፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት፣ በአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትስስር ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ደረጃና ተጓዳኝ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዳዮችም የውይይቱ አካል ናቸው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጉባኤው በትብብር ላይ የተመሰረተ አህጉራዊ የዲጂታል ትራንስፈርሜሽን ለማፋጠን የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ አህጉራዊ የዲጂታል ትራንስፈርሜሽን ለማፋጠን በአህጉሪቱ ያለው 70 ከመቶ በላይ ወጣት ኃይል ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የዲጂታል ክህሎትና የመሰረተ ልማት ግንባታን በማፋጠን 43 ከመቶ ብቻ የሆነውን የአህጉሪቷን ኢንተርኔት ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር ማሳደግ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
ከዚህ አንጻር፤ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ በሰጠችው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ በቴሌኮም ዘርፍ፣ በብሔራዊ መታወቂያ፣ በዲጂታል የክፍያ ሥነ-ምህዳርን በማስፋት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ አስችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ዘላቂና ፍትሕዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥርዓትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ፤ የአህጉሪቷን ዜጎች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
ጉባኤውም አህጉራዊ የዲጂታል ሥርዓትን በማሻሻል በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ቴሌኮም ሕብረት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ልማት ቢሮ ዳይሬክተር ኮስማስ ላኪሶን ዛቫዛቫ፤ የአህጉሪቷን እድገት ማፋጠን ሚያስችል የዲጂታል መሰረተ ልማት በመዘርጋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የዜጎችን የዲጂታል ተጠቃሚነት ለማሳደግም ትርጉም ያለውና ተመጣጣኝ የኢንተርኔት አገልግሎት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን የሚሆኑ ዜጎች ኢንተርኔት እንደማይጠቀሙ ጠቅሰው፤ ከዚህም አፍሪካ ትልቁን ድርሻ እንደምትወስድ ጠቁመዋል።
በመሆኑም በአፍሪካና በሌሎች አህጉር የዲጂታል ተጠቃሚነትን ለማሳደግም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኅብረቱ ጉባኤው ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ አባል አገራት ሚኒስትሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት፣ የልማት አጋር ድርጅቶች ተወካዮችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ የጀመረው የዓለም አቀፍ ቴሌኮም ሕብረት ጉባኤ እስከ መስከረም 24/2016 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
ዋና መሥሪያ ቤቱን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው የዓለም አቀፍ ቴሌኮም ሕብረት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1865 የተመሰረተ የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም ነው።
ሕብረቱም ኢትዮጵያን ጨምሮ 193 አባል አገራት ያሉት ሲሆን ዓለም አቀፍ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ትስስርን የማፋጠን ግብ በመያዝ እየሰራ ነው።