በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገጽታ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገጽታ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016 (ኢዜአ)፦ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገጽታ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ከመስከረም 20 እስከ ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚኖረውን የአየር ሁኔታ በማስመልከት ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ መግለጫ ልኳል።
በመግለጫውም በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገጽታ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።
በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገጽታ የተሻለ ይሆናል ብሏል።
የአየር ሁኔታው በሂደት ወደ ደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ እርጥበት እንደሚኖረው አስታውቋል።
በመሆኑም ወቅታዊ ዝናብ ማግኝት በሚጀምሩና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት የደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀደም ብሎ የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ መሆኑን አመላክቷል።
እርጥበታማው የአየር ሁኔታ ወደ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የሚያደርግው መስፋፋት በአካባቢው ለሚኖሩ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥሩ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
በተመሳሳይ በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የዝናቡ ሁኔታ ቀጣይነት የሚኖረው በመሆኑ ቀደም ብለው ለተዘሩና አልፎ አልፎ ፍሬ በመሙላት ላይ ለሚገኙ ሰብሎችም እርጥበታቸውን ጠብቀው ላመቆየት እንደሚረዳ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ዘግይተው ለተዘሩና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎች የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት ጠቃሚ መሆኑን ጠቁሟል።