ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ።  

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአንድ ዓመት ከሰባት ወራት የሥራ እንቅስቃሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ከፍትኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ውይይት ተደርጎበታል።


 

በውይይቱም የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር የእስካሁን የሥራ አፈጻጸምን ያቀረቡ ሲሆን በዚህም በአምስት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ መከናወኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ምክር ቤቱ ኮሚሽኑን ገለልተኛ ተቋም አድርጎ ማቋቋሙን አስታውሰዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ ዕቅድና ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሥራዎችን በአራት ምዕራፍ ማለትም የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የትግበራና የማጠቃለያና የግብረ መልስ በሚል ከፋፍሎ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም በቅድመ ዝግጅትና በዝግጅት ስራዎች ለምክክሩ መሰረት የሚጥሉ ተግባራት በጥሩ ሁኔታ መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም በአምስት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከወረዳ ጀምሮ የተሳታፊና የአስተባባሪ እንዲሁም የአጀንዳ ልየታ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የፀጥታ ችግር ባለባቸው እንደ አማራና ኦሮሚያ ባሉ አካባቢዎች በቀጣይ ምክር ቤቱና የምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

ለዚህም ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሲቋቋም ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ልሂቃንና የመንግስት አጀንዳና ምክክር ብቻውን ዘላቂ መፍትሄ ባለመምጣቱ መላው ዜጋ የተሳተፈበት የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክር የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኑን በማንሳት አጀንዳ አፍላቂውም ምክክር አድራጊውም ህዝብ ነው ብለዋል።

መንግስት ለምክክሩ ስኬታማነት ድጋፍ የማድረግ እንጂ አጀንዳ ሰጪ አይደለም ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ህዝብ ተመካክሮ የሚደርስባቸውን ውሳኔዎች መንግስት ይቀበላል ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ በዚህ ዓመት አጋማሽ እንደሚካሄድ በመጠቆም ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግስት አስተማማኝና ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ ሰላምን የማስፈን ስራን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የነቃ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ፤ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የመንግስትነት ታሪክ ያላት ብትሆንም በበርካታ ጉዳዮች መግባባት ያልተደረሰበትና የሀገር ግንባታ ሂደቱም ያላለቀ ነው ብለዋል።


 

በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ልዩነትም ሀገሪቱን በግጭትና ወደ ኋላ በሚጎትቱ ሁኔታዎች እንድታልፍ ማድረጉን ነው የጠቀሱት።

መንግስት ኢትዮጵያን ለከፋ ቀውስ የዳረጉ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለማስወገድና በጋራ ቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበትና በገለልተኛነት የሚካሄድ ምክክር ለማካሄድ ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ወዲህ በዝግጅት ስራዎቹ አካታችነትን በማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት መልካም መሆኑን የህግ አውጭው ምክር ቤት ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ዋናው ሀገራዊ ምክክር በስኬት እንዲካሄድ መሰረት የጣለ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመለትን ዓላማ በስኬት እንዲያከናውን በአትኩሮት ይሰራል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ እንዳሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የተጣለበትን ሀገራዊ አደራ እንዲወጣ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዚህም የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ስራዎችን በውጤታማነት ለማከናወን ተገቢ እቅድ አውጥተው እየተገበሩ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴ ተቋቁሞ ክትትል ሲደረግ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የምክክር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታና አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ባላካሄደባቸው ክልሎች ስራውን በአፋጣኝ አጠናቅቆ ወደ ዋናው ምክክር እንዲገባ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም