ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአምስት ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ ማካሄዱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአምስት ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ ማካሄዱን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአምስት ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ ማካሄዱን ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች ጋር የኮሚሽኑን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው ሂደት አሳታፊ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ተግባራትን ሲያከናወን ቆይቷል።
በዚህም ኮሚሽኑ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረጉን ጠቅሰው፤ የዛሬው መድረክም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ መንግሥት ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ተገንዝቦ ለቀጣይ ሥራዎች የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ለማስቻል መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ኮሚሽኑ አሁን ላይ በአምስት ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ይህ ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሂሩት ገብረስላሴ በበኩላቸው በመድረኩ ፍሬያማ ውይይት የተደረገበት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም መንግስት የኮሚሽኑ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር በሀገራዊ ምክክሩ መግባባት ላይ የሚደረስባቸው ሃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጦልናል ብለዋል፡፡
ይህም ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል የገቢዎች ሚኒስትሯ ዓይናለም ንጉሴ፤ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግስት እስከታችኛው እርከን ድረስ ባሉት መዋቅሮቹ አማካኝነት ለኮሚሽኑ ስራዎች ስኬት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም እንደ አንድ ባለድርሻ አካል መንግስት በምክክሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ የበኩሉን ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በተለይ ሂደቱን አሳታፊና ገለልተኛ ለማድረግ ያከናወናቸው ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኮሚሽኑን ስራዎች መደገፍ አገርን መደገፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
መንግስት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ኮሚሽኑን ከማቋቋም ጀምሮ ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታውሰው፤ ከዚህ አኳያ ለኮሚሽኑ ስራዎች ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በምክክሩ ኢትዮጵያዊያን የተስማሙባቸውን ሃሳቦች ገቢራዊ ለማድረግ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡