ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል - የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል - የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እንዲሁም በምክክሩም ንቁ ተሳታፊ ለመሆን ዝግጅት ማድረጉን የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች ጋር የኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ኮሚሽኑ እስከ አሁን ያከናወናቸው ሥራዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በመድረኩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ አደም ፋራህ፤ ኮሚሽኑ የተሳካ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ እስካሁን ያከናወናቸው ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
በተለይም አገራዊ ምክክሩ አካታችና ሁሉን አሳታፊ ለማድረግ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ለማረጋገጥ የተኼደበት ርቀትና አጠቃላይ ጥረቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ነው ያነሱት።
በቀጣይም "ከማን ምን ይጠበቃል" የሚለውን በመለየትና ቀሪ ሥራዎችን በተሳካ መልኩ ለማከናወን ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያየ መሆኑን በገለጻው ለመረዳት ማቻላቸውን ተናግረዋል።
አገራዊ ምክክሩ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የብልጽግና ጉዞዋን ለማፋጠን እንደሚያስችል ጠቁመው፤ ከዚህ አኳያ ከብልጽግና ፓርቲ አባላት ጋር በተካሄደ ሰፊ ውይይት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ብልጽግና ፓርቲ እንደ ገዥ ፓርቲ የሚጠበቅበትን ድጋፍ በየደረጃው በሚገኙ የፓርቲ አመራሮች በኩል እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፓርቲው ለኮሚሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡
ፓርቲው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በአገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ ለመሆንና አገራዊ ምክክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የምክክር ውጤቱን ገቢራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡