በአዲስ አበባ በሰው ተኮር መርሃ ግብር 750 ህጻናት በቋሚነት እየተደገፉ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ በሰው ተኮር መርሃ ግብር 750 ህጻናት በቋሚነት እየተደገፉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። 

ከንቲባዋ "አንድ ቤተሰብ ለአንድ ህጻን" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀውን የዘላቂ ድጋፍ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምረዋል። 

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው መርሃ ግብር በተለይም ልጆች ዘላቂ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ተብሏል።    

በዛሬው ዕለትም አንድ ባለሃብት እስከ 6 ዓመት እድሜ ያላቸውን 100 ህጻናት የከፍተኛ ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ሃላፊነቱን ወስደው ስምምነት ፈርመዋል።          
      

ለድጋፍ መርሃ ግብሩም ባለሃብቱ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ከህብረተሰብ ተሳትፎና  በጎ ፈቀድ ማስተባሪያ ኮሚሽን ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት ባለሃብቱ በየወሩ ለህፃናቱ ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቀድ ማስተባሪያ ኮሚሽን ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ ይሆናል።  

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ባለሃብቱ ያደረጉት ድጋፍ ለሌሎችም አርአያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል።  

መንግሥት  ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተለይም ሰው ተኮር ልማት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ ለ750 ህጻናት ዘላቂነት ያለው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ወገኖች በብዙ መልኩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ከንቲባዋ አረጋግጠዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብርሃም ታደሰ፤ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አቅም የሌላቸው ወላጆች ተለይተው ከ3 ወር እስከ 3 ዓመት ድረስ ላሉ ልጆቻቸው ዘላቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

በዛሬው እለትም ባለሃብቱ ያደረጉት ድጋፍ ከተማ አስተዳደሩ ለጀመረው ሰው ተኮር ልማት የላቀ ትርጉም አለው ሲሉ ተናግረዋል።  

የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑ ወላጆችም ለተደረገላቸው ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

         

 

    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም