የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የልማት አጋር ነው -የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የልማት አጋር ነው -የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016(ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሕብረት የተለያዩ የልማት መርሐ-ግብሮችን በማከናወንና በመደገፍ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የልማት አጋር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን፤ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።
በዛሬው እለትም ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጋር በሁለትዮሽ ትብብርና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በቆይታቸው የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረትን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ሕብረቱ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት መርሐ-ግብሮችን በመቅረጽ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለት ይፋ የሚደረገው የሕብረቱ የ650 ሚሊዮን ዩሮ የባለ ብዙ ዘርፍ ዓመታዊ የድጋፍ መርሐ-ግብርም የሁለቱን ወገኖች ስትራቴጂካዊ ትብብር ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን፤ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ የመጡባቸውን አይነተኛ ጉዳዮች አንስተዋል።
የጉብኝቱ አላማ በ18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ፣ ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እና ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ስትራቴጂካዊ አጋር ናት ያሉት ኮሚሽነሯ የዚሁ ትብብር አካል የሆነው የ650 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ማዕቀፍ ዛሬ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ድጋፉ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ግብርና ስራዎች፣ ብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት፣ አካባቢ ጥበቃና ታዳሽ ኃይል ልማት፣ ለሰው ኃይል ልማት እንዲሁም አስተዳደር፣ ሰላም ግንባታና የዴሞክራሲ ልማት ስራዎች እንደሚውልም ነው የጠቆሙት።
ድጋፉ የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል እ.አ.አ በሕዳር ወር 2023 በቤልጂየም ብራስልስ የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪካ ሕብረት የሚኒስትሮች ስብስባ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
ስብስባው ሕብረቱ እ.አ.አ በ2022 ይፋ ያደረገው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ስትራቴጂ አፈጻጸምና በሌሎች የተቋማቱ የትብብር ስራዎች ላይ እንደሚመክርም አመልክተዋል።
ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን በቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ አመራሮችና ቀጣናዊ ልዑካን ጋር ይወያያሉ ተብሏል።