የአፍሪካን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ አፍሪካውያን በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ አፍሪካውያን በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ ፤መስከረም 22/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ አፍሪካውያን በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።
" ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለዘላቂና ፍትሐዊ መጻኢ ጊዜ፤ የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው በአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣትና የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየመከረ ይገኛል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ አፍሪካ 70 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ወጥቶች የሚኖሩበት አህጉር በመሆኑ የዲጂታል ሽግግርን ለማምጣት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በአፍሪካ 43 ከመቶ ብቻ ናቸው የኢንተርኔት ተደራሽነት ያላቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ዜጎችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ መሰረተ ልማት እና የዲጂታል ክህሎት ግንባታ ላይ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የአለም አቀፉ የሌኮም ህብረት የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ቢሮ ዳይሬክተር ኮስማስ ዛቫዛቫ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለሁሉን አቀፍ እድገት አቀጣጣይ በመሆኑ በአፍሪካ ትርጉም ያለው የኢንተርኔት መሰረተ ልማት በመዘርጋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር)፣ በበኩላቸው አፍሪካውያን ለአፍሪካ የተሻለ መፃኢ ጊዜ በጋራ መስራት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ እስከ መስከረም 24/2016 ዓም የሚቀጥል ሲሆን ኢትዮጵያ በዘርፉ ያደረጋቻቸው የማሻሻያ ስራዎች ተብራርተውበታል።