ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኢንኩቤሽን ማዕከል በቻይና ከፈተ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ከቻይና አለማቀፍ የንግድ ትብብር እና ትስስር ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት የመጀመሪያውን ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኢንኩቤሽን ማዕከል በቻይና ከፈተ።

ማህበሩ ማዕከሉን የከፈተው በሁናን ግዛት ቻንግሻ ከተማ በቻይና-አፍሪካ የወጣቶች የኢኖቬሽን እና ኢንተርፕረነርሺፕ ቤዝ ሃይ-ቴክ ዞን ላይ ነው። 

ማዕከሉ በቻይና እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያበረታታ ሲሆን በወጣት ስራ ፈጣሪዎች መካከል በኢኖቬሽን፣ በቴክኖሎጂ እና በስራ ፈጠራ ተቀናጅተው እንዲሰሩ እድል ይፈጥራል ተብሏል። 


 

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የቻይናዋ ሁናን ግዛት የንግድና ገበያ ቁጥጥር ቢሮ ተመራማሪ እና የዓለም አቀፉ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ልውውጥ ማዕከል ዳይሬክተር ሊ ዌይሚን እንዳሉት የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኢንኩቤሽን ማዕከል በቻይና አፍሪካ የመጀመሪያ የወጣቶች ኢኖቬሽን እና ስራ ፈጠራ ማዕከል ነው ብለዋል።

ማእከሉ የአፍሪካ የንግድ ተቋማትንና ከአፍሪካ ጋር በትብብር የሚሠሩ የቻይና ኢንተርፕራይዞችን እንደሚያስተሳስር ገልጸው በቻይና እና በአፍሪካ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞችን ለማስተዋወቅ ያግዛል ብለዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዲፓርትመንት ምክትል ሀላፊ አቶ ይስሀቅ ሽመልስ በበኩላቸው  ስምምነቱ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በንግድ ማስተዋወቅ ረገድ እድሎችን ይፈጥራል ብለዋል።

ኢምባሲው ከማህበሩ ጎን በመሆን ወጣቶችን ዋና ተዋናይ በማድረግ የሁለቱ ሀገራትን ኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝምን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።


 

የኢትየጵያ ስራ ፈጣሪ ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሪት ሳሚያ አብዱልቃድር ማህበሩ ስራ ፈጠራን ለማስተዋወቅ፣ ለመደገፍ፣ ወጣቶች ራዕያቸውን ዕውን የሚያደርጉበት ምቹ ስነምህዳር እንዲፈጠር በወጣት ስራ ፈጣሪዎች እ.አ.አ በ2020 መቋቋሙን አስታውሳለች።

ማህበሩ ከሀገር ውስጥም ውጭም ካሉ መንግስታዊ፣መንግስታዊ ካልሆኑ፣ የልማት አጋር ተቋማት እና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አክላለች።

የማህበሩ አባላት በግብርና፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ቱሪዝም፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ሌሎች መስኮች ላይ በመሰማራት እየሰሩ እንደሚገኙም ነው የማህበሩ ፕሬዝዳንት የገለጸችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም