ቀጥታ፡

በሪጋ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ውጤት አስመዝግቦ ለተመለሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ሽልማት ተበረከተለት

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 22/2016 (ኢዜአ)፦ ለመጀመሪያ ጊዜ በላቲቪያ ሪጋ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ  ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ  የእውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

በዓለም የጎዳና ላይ ውድድር ለተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ዛሬ ማለዳ ላይ ሀገሩ ሲገባ በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

በዓለም የጎዳና ላይ ውድድር በሁለት ወርቅ በአራት ብር እና በአንድ ነሐስ በድምሩ ሰባት ሜዳልያዎችን በማግኘት ውድድሩን በሁለተኝነት ላጠናቀቀው የአትሌቲክስ ቡድኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስካይ ላይት ሆቴል እውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።

ፌድሬሽኑ በውድድሩ ወርቅ ላመጡ አትሌቶች የ45 ሺህ ብር፣ የብር ሜዳልያ ላስገኙ የ30 ሺህ ብር፣ ነሐስ ላመጡ ደግሞ የ15 ሺህ ብር እንዲሁም ዲፕሎማ ላመጡ አትሌቶች ደግሞ የ10 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም