ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ የ2016 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ተጀመረ

ጎንደር ፤ መስከረም 21/2016 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ በሚገኙ 83 የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የ2016 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ዛሬ በይፋ መጀመሩን  የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በከተማው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ ከ155 ሺህ በላይ የመማሪያ መጻህፍት ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ መሆኑንም መምሪያው ገልጿል፡፡

በትምህርት ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመምሪያው ሃላፊ አቶ ዳንኤል ውበት እንዳስታወቁት፤ በከተማው የሰፈነው ሰላም ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡


 

በአዲሱ የትምህርት ዘመን በቅድመ መደበኛ፣ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ90 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ዘመኑ በአማራ ልማት ማህበር (አልማ) እና በሌሎች አጋር አካላት የገንዘብ ድጋፍ የተገነቡ 64 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ለመማር ማስተማር ሥራው ዝግጁ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች 15 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የመማሪያ ቁሳቁስ ከተለያዩ ድርጅቶችና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ተሰባስቦ መከፋፈሉንም ሃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

የመምሪያው ሃላፊ እንዳሉት፤ በከተማው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የታተሙ ከ155 ሺህ በላይ የመማሪያ መጻህፍት ለ65 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

በከተማው የቀበሌ 02 አንደኛና ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ከ300 በላይ ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ማሩ አድማሱ ናቸው፡፡

በከተማው የሰፈነው  ሰላም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መጥተው ትምህርታቸውን መጀመር እንዳስቻላቸው አስታውቀዋል፡፡

''እኛ ተማሪዎች የወደፊት ህልማችንን ለማሳካት ከምንም በላይ ሰላም እንሻለን'' ያለችው የዚሁ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ኤፍራታ ዳዊት ናት፡፡

ሌላዋ ተማሪ ህይወት አደራ በበኩሏ፤ ''የሰላም ዋጋ ከፍ ያለ ነው ትምህርት ደግሞ ሰላምን ይሻል ትምህርት ቤቴ በመከፈቱ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል'' ብላለች።

ትምህርቷን ጠንክራ በመከታተል ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀቷንም ገልጻለች፡፡

በከተማው የዘመኑ ትምህርት ማስጀመሪያ ሥነ- ሥርዓት ላይ ወላጆች፣ መምህራንና የትምህርት አመራሮች መገኘታቸው  ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም