የውጭ አገራት የስራ ስምሪት የሀገርን ፍላጎትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ከተለያዩ አገራት ጋር እየሰራ ነው - የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ አገራት የስራ ስምሪት የሀገርን ፍላጎትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ከተለያዩ አገራት ጋር እየሰራ ነው - የስራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2016 (ኢዜአ)፦ የውጭ አገራት የስራ ስምሪት የሀገርን ፍላጎትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ከተለያዩ አገራት ጋር እየሰራ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
ሁለተኛው አህጉር አቀፍ የአፍሪካ የሰው ሃብት ልማትና የስራ እድል ፈጠራ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ በጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ.)፣ በኤቲዲ ኢትዮጵያና በዘ-አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት ትብብር መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት ሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ፤ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ የውጭ አገራት የስራ ስምሪት ላይ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በውጭ አገራት የስራ ስምሪቱ የሀገርን ፍላጎትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ከተለያዩ አገራት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጉባኤውም መዘጋጀት በተለይም በውጭ አገራት የስራ ስምሪትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የተሞክሮ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፤ ኢትዮጵያ ትኩረት ከምትሰጣቸው የልማት መስኮች መካከል የሰው ሀብት ልማት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በዘርፉ ያለውን አቅም ለማሳደግ የትምህርትና ስልጠና መስኮችን የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክህሎት ልማት ኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢና የዘ-አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ገመቹ ዋቅቶላ፤ በውጭ አገራት የስራ ስምሪት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሁኑ ሙያና ክህሎት ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በክህሎት ልማት ላይ ለሚደረገው ጥረት ስኬት ኢንስቲትዩቱ የበኩሉን ሚና መወጣቱን ይቀጥላል ነው ያሉት።።
የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ) የኢትዮ-ጀርመን ዘላቂ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራም ማናጀር ላሪስ ፊቼል፤ ጀርመን የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ለማጎልበትና በስራ እድል ፈጠራ ለኢትዮጵያ ድጋፍና ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በጉባኤውም የውጭ አገራት የሥራ ስምሪትን ለማሻሻል የሚረዱ የሥራ ፍላጎትና አቅርቦት፣ የትምህርትና ስራ ሽግግር፣ የዲጂታል ሥርዓት የሥራና ክህሎት እድልና ፈተና፣ የኢንዱስትሪና የትምህርት ተቋማት ትስስር፣ በሰው ኃይል ልማት የግሉ ዘርፍ ያለው ሚና እና የቀጣይ የዓለም የስራ ሁኔታ አዝማሚያ ላይ ያተኮሩ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ የመንግስታቱ ድርጅትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም አጋር አካላት እየተሳተፉ ነው።