በስልጤ ዞን የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን በስፋት የማስተዋወቅና የሃብት ምንጭ የማድረግ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል- የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ - ኢዜአ አማርኛ
በስልጤ ዞን የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን በስፋት የማስተዋወቅና የሃብት ምንጭ የማድረግ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል- የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/ 2016(ኢዜአ)፡- በስልጤ ዞን የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን በስፋት የማስተዋወቅና የሃብት ምንጭ የማድረግ ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።
በስልጤ ዞን የሀረሸይጣን ሀይቅ፣ አባያ ጡፋ ሀይቅ፣ ሙጎ ተራራ፣ የአሳኖ ትክል ድንጋይ፣ አልከሶ መስጅድ፣ የሀጂ አሊዩ መካነ መቃብርና ሌሎችም የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ።
የተፈጥሮ ፍል ውሃና አስደናቂ መልክአ ምድር፣ በአእዋፋት፣ በራጋ ማጋ ባህላዊ የግጭት አፈታትና በሌሎችም ይታወቃል።
እነዚህን ሃብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አሊ ከድር ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ለኢኮኖሚ ልማትና ለስራ እድል ፈጠራ የላቀ ድርሻ እንዲኖራቸው እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን በስፋት የማስተዋወቅና የሃብት ምንጭ የማድረግ ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የራጋ ማጋ ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት በአካባቢው የመከባበርና የመቻቻል መገለጫዎች አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
የስልጤ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልትን በአግባቡ በመሰነድ ማስተዋወቅና የጋራ ሃብት አድርጎ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ይርዳው ናስር፤ በዞኑ የሚገኙ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የቱሪዝም ትምህርት ክፍል መምህር በቀለ ኡማ፤ በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም የሚያስችል የጉዞ ጥቅል ስራ ላይ መዋሉንም ጠቅሰዋል።