ቀጥታ፡

የዜጎችን ጤና በመጠበቅ ለአገር ግንባታና ዘላቂ ልማት በጋራ መስራት ይገባል- ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/ 2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ አይነተኛ የጤና ችግር መንስኤዎችን በመለየት የዜጎችን ጤና በመጠበቅ ለአገር ግንባታና ዘላቂ ልማት በጋራ መስራት ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።        

አራተኛው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ፎረም "ጠንካራ አጋርነት፤ትርጉም ያለው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ተሳትፎ ለተሻለ ጤና" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።  

አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች አገር ገንቢ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት በምን መልኩ ሊቀናጁ ይገባል? የወጣቶች ኃላፊነትስ ምን ሊሆን ይገባል? የሚሉና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተዘጋጀ መድረክ መሆኑ ታውቋል። 

በመድረኩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት በማደግ ላይ ባሉ አገራት በተለያዩ የጤና መጓደል ምክንያቶች የሰዎች የሞት ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ለአገር የኢኮኖሚ እድገትና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የጤና ችግር መንስኤዎችን በመለየት ለመፍትሄው በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በአገር ግንባታና የሚፈለገውን እድገት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የዜጎችን ጤንነት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል። 

የአፍላ ወጣቶችን እርግዝና እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለመከላከል አሁን ካለበት 13 በመቶ እኤአ በ2030 በግማሽ ለመቀነስ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የሱስና ተያያዥ የአዕምሮ ጤና ችግሮችን፣ ተላላፊና ያልሆኑ የጤና ችግሮችን ለመቀነስም በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
        

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በአገሪቷ ከ3 ሺህ ያላነሱ የወጣት ማዕከላት መኖራቸውን ጠቅሰው በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ የአካል ጉዳት ያለባቸው ወጣቶች ልዩ ትኩረት የሚሹ በመሆኑ በዚህም ላይ የበለጠ ለመስራት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።   

ለወጣቶች የሥነ ልቦና ድጋፍና ሌሎችንም የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግም በቅንጀት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል። 

የዓለም የጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሮዝ ዲላሚኒ፤ በወጣቶች ጤና ዙሪያ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ስራዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

የወጣቶችን ጤና ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረትም የዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።  

የኢትዮጵያ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወጣት ቶፊክ እስማኤል፤ ለወጣቶች ጤና መጠበቅ በምክር ቤቱ በኩል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግሯል።    

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም