ቀጥታ፡

ታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችላቸውን  አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/ 2016(ኢዜአ)፡-  ታዳጊ  ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችላቸውን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ።

አህጉር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መድረክ ላይ  ከ18  የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 150 ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን፤ ታዳጊ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ እየደረሰባቸው ያለውን ተጽኖ ለመቋቋም የሚያስችል አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በቀጣይ ቀናት በሚኖረው በዚህ ጉባኤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ልምድና ተሞክሮ ለመድረኩ ተሳታፊዎች እንደሚቀርብም ተገልጿል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሰንዶካን ደበበ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አፍሪካ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ሚናዋ ጥቂት ቢሆንም  ግንባር ቀደም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆናለች ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአስር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ውስጥም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአህጉር አቀፍ ደረጃም ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም በተለይ ታዳጊ ሀገራት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የግሎባል ኢንቫይሮንመት ፋሲሊቲ ተወካይና ዓለም አቀፍ የአካባቢ ስምምነቶች ድርድር ማስተባበሪያ ዳይሬክተር መንሱር ደሴ በበከላቸው፤ ጉባኤው በአነስተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ለማስቻል መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡l
 

በዚህም ታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመመከት የሚተገብሯቸውን ፕሮጀክቶች ላይ የጋራ ምክክር በማድረግ አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

በግሎባል ኢንቫይሮመንት ፋሲሊቲ አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ ጃሶን ስፔንስሌይ፤ ግሎባል ኢንቫይሮመንት ፋሲሊቲ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የአካባቢ መራቆትን ፣የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሃ ህይወት መመናመንን ለመቆጣጠር መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዚህም በተለይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ችግሩን ለመቋቋም በሚያደርጉት ጥረት ላይ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የገለጹት፡፡ 

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር አማካኝነት 32 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመቋቋም እየሰራች መሆኑ ይታወቃል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም