ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ቅርሶችን እና የቱሪስት መስህቦችን በማልማትና በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ይሰራል

ድሬዳዋ፤ መስከረም 21/2016 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳደር ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ቅርሶችን እና መስህቦችን በማልማትና በመንከባከብ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የኢፌዴሪ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ለ56 የድሬዳዋ ቅርሶች ዕውቅና መስጠቱ ከዘርፉ ዘላቂ ጥቅም ለማግኘት እንደሚያግዝም ተመልክቷል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ገበየሁ ወጋየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ መስህቦችንና ቅርሶችን በማልማትና በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ለዚህም የቱሪስት መዳረሻ የሆኑና ሺህ ዘመናት ዕድሜ ያስቆጠሩ ታሪካዊ ቅርሶችና መስህቦችን ለቱሪስት ምቹና ማራኪ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ሥራዎቹ እየተከናወኑ ያሉት ከኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን በተገኘ 14 ሚሊዮን ብር መሆኑንም አቶ ገበየሁ ጠቅሰዋል። 

በተለይ የድሬዳዋ የባቡር ትራንስፖርት ጣቢያን ለቱሪስት ምቹ ለማድረግ የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ነው ያስታወቁት።

አቶ ገበየሁ እንዳሉት አስተዳደሩ ድሬዳዋን አገር አቀፍ ተመራጭ የቱሪዝም ኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ በ2 ቢሊዮን ብር ዘመናዊና ግዙፍ የሲቪክ ማዕከል እየገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ማዕከሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ አዳራሾች፣ የፊልም እና የቴአትር ማሳያዎችን አካቶ እየተገነባ ሲሆን  በሚቀጥለው ዓመት ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። 

በፅህፈት ቤቱ የመረጃ ባለሙያ አቶ ደረጀ አበራ በበኩላቸው፣ በድሬዳዋ ታሪካዊ ቅርሶችን ጨምሮ ሰው ሰራሽ መስህቦችና ቅርሶች በተገቢው መንገድ ለምተው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ከሚኒስቴር ተቋማት፣ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣንና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት  እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።

"ለአብነት የ16ተኛው ክፍለ ዘመን የስልጣኔና የንግድ ማዕከል የነበረችውን የሐርላ ማህበረሰብ መንደር  ለቱሪስት ተደራሽ ለማድረግ በሀርላ ቀበሌ አነስተኛ ሙዚየም መገንባቱን ገልጸዋል።

አቶ ደረጀ እንዳሉት ባለፉት አምስት ዓመታት በድሬዳዋ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እየተበራከቱ መምጣት ለቱሪዝም ዘርፍ መጎልበት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።

በድሬዳዋ ከተመዘገቡት 80 ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች መካከል የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ለ56ቱ ዕውቅና መስጠቱ ቅርሶች ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ፣ እንዲጠበቁና ከዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማግኘት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በዘርፉ የተከናወኑ ሥራዎች ወደ ድሬዳዋ የሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰትን በመጨመር የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ማስቻሉንም አቶ ደረጀ ገልጸዋል።

ለአብነትም ባለፈው ዓመት ወደ ድሬዳዋ ከመጡ 131 ሺህ 620 የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች 526 ሚሊዮን 504 ሺህ ብር  ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም