ኢትዮጵያ ከቅመማ ቅመም ምርት ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቅመማ ቅመም ምርት ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ተገለፀ
ቦንጋ ፤ መስከረም 21/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከቅመማ ቅመም ምርት ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ልማት ባለሥልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ልማት ባለሥልጣን የቅመማ ቅመም ልማት ዴስክ ሀላፊ አቶ ሞገስ አሸናፊ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያ የቅመማ ቅመም ሰብል ጥንታዊ ቢሆንም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከተጀመረ ግን ገና ከስድስት ዓመት ያልዘለለ እድሜ ነው ያለው።
ዘርፉ ለዘመናት ከዘልማድ አሰራር የተላቀቀ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ሀገር ከዘርፉ መጠቀም የሚገባትን ያህል ሳታገኝ መቆየቷን ገልፀው፣ ይህንን ለመቀየርም በምርምር 19 የቅመማ ቅመም ፓኬጆች መቀረፃቸውንም ጠቁመዋል።
ከነዚም ውስጥ ስምንቱ ቀድመው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን 11ዱ ደግሞ በህትመት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህን ወደ ሥራ በማስገባት እና የአምራቹን ግንዛቤ በመቀየር ምርቱን በጥራትና በስፋት በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዚህም ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ለውጭ ገበያ ይቀርቡ በነበሩ የዝንጅብል፣ የበርበሬ እና የእርድ ምርቶች ላይ የጥራት መጓደል በመስተዋሉ ተፈላጊነቱ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመው፣ ይህንና መሰል የገበያ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ መመሪያዎችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሰራ ነውም ብለዋል።
ዘርፉን ከችግር ለማውጣት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ባለሥልጣኑ እንደሚሰራ አቶ ሞገስ ጠቁመዋል።
ለቅመማ ቅመም ምርት ትልቅ አቅም ካላቸው ክልሎች መካከል አንዱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መሆኑን የገለፁት የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጀብ ናቸው።
በክልሉ ከ88 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በኮረሪማ፣ በቁንዶ በርበሬ፣ በበርበሬ፣ በእርድና በሌሎች የቅመማ ቅመም ምርቶች መሸፈኑን ጠቁመዋል።
ዘርፉ በጠባብ መሬት ላይ ብዙ ምርት እና ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ የበርካቶችን ህይወት ሊቀይር እንደሚችል ተናግረዋል።
በቀጣይም እንደ ቡና ሁሉ ለቅመማ ቅመም ምርት ልዩ ትኩረት በመስጠት ምርቱን በስፋትና በጥራት በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አቶ በላይ ጠቁመዋል።
የቅመማ ቅመም ምርት ከሚያስገኘው ከፍተኛ ገቢ በተጨማሪ በመድሀኒትነት የሚያገለግል በመሆኑ ልማቱን ወደ ደጋማ የክልሉ አካባቢዎች የማስፋት ሥራ እንደሚሰራ አቶ በላይ ተናግረዋል።
ክልሉ ለቅመማ ቅመም ምርት ምቹ ሥነ ምህዳርና የአየር ጠባይ ያለው ቢሆንም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ መሀመድ ሳኒ አሚን ናቸው።
ክልሉ ከዘርፉ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ ጠቁመው ለአብነትም ሂደቱ ከክልል እስከ ወረዳ በጠንካራ የሰው ሀይል እንዲመራ ተደርጎ ተፈላጊ የሆኑ የቅመማ ቅመም ምርቶችን ለይቶ የማልማት ሥራ ሊጠቀስ እንደሚችል አንስተዋል።
በዚሁ መሰረት ጠንካራ ክትትል ማድረግ የሚችሉና የዘርፉ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን በመመደብ ከ10 በላይ የተለያዩ የቅመማ ቅመም አይነቶች ተለይተው በትኩረት እየተሰራባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
በተለይም በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች ምርቱ በስፋት እንደሚመረት የጠቆሙት አቶ መሀመድ ሳኒ፣ ጥራት ያለው ምርት በማምረት ከሀገርም አልፎ ለውጭ ሀገር ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት እንደ ሀገር 300 ሺህ ሄክታር የነበረውን የቅመማ ቅመም ምርት ሽፋን ከ802 ሺህ ሄክታር በላይ ማድረስ መቻሉን ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን የገኘነው መረጃ ያስረዳል።