የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓልን ስናከብር ሰላም፣ፍቅርና አንድነትን በሚያጠናክር መነሳሳት ሊሆን ይገባል- ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ - ኢዜአ አማርኛ
የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓልን ስናከብር ሰላም፣ፍቅርና አንድነትን በሚያጠናክር መነሳሳት ሊሆን ይገባል- ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ

ደሴ ፤ መስከረም 21 / 2016(ኢዜአ)፡- የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓልን ስናከብር ሰላምን ፍቅርንና አንድነትን ለማጠናከር በመነሳሳት ሊሆን ይገባል ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ገለጹ።
በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓል በደማቅ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት ዛሬ ተከብሯል፡፡
ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ በንግስ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ሁሉም ህዝብ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ግሸን ደብረ ከርቤ ያረፈው መስቀል የሚያስተምረን ፍቅርን፣ አንድነትንና አብሮነትን በመስበክ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ችግሮችን በውይይትና በንግግር በመፍታት ለሀሳብ የበላይነትና ልዕልና ማበብ መስራት አለብን ብለዋል።
የንግስ በዓልን ስናከብር ሰላምን ፍቅርንና አንድነትን ለማጠናከር በመነሳሳት ሊሆን ይገባል ያሉት ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ፤ የንግስ በዓሉ ባማረ ሁኔታ በድምቀት እንዲከበር ላስተባበሩና በቦታው ለተገኙ ምዕምናን ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፈራው እንደገለጹት፤ በዓሉን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊ የቅደመ ዝግጅት ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መስራት ተችሏል።
በዓሉ ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት ቦታ ላይ መከበሩ ለምዕመኑ ታላቅ በረከት የሚያስገኝ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሰላምን በሀገር ለማስፈን የተጸለየበት መሆኑን አስረድተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮንን በበኩላቸው፤ በዞኑ ካሉ ባህላዊ፣ ሐይማኖታዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች መካከል በየዓመቱ መስከረም 21 የሚከበረው የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዓሉ በሰላምና በድምቀት እየተከበረ ዛሬ ላይ በመድረሱ ይህንኑ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
መንግስት የመንገድ፣ የውሃና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ምዕመኑ በዓሉን በቦታው በመገኘት በሰላም እንዲያከብሩ የድርሻውን መወጣቱን ተናግረዋል።
የንግስ በዓሉን በቀጣይነት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች በማስተዋወቅ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
በበዓሉ ላይ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች፣ የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮችና በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።