ቀጥታ፡

መንግስት የተፈጥሮ ሀብቶችን በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው- የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች

ሚዛን አማን፤መስከረም 21/2016(ኢዜአ)፡- መንግስት "በገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክት የተፈጥሮ ሀብቶችን በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለው እንቅስቃሴ ሊበረታታ ይገባል ሲሉ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር በበኩሉ የደንቢ ሀይቅ ሎጅ ግንባታ፤ በግንባታ ሂደቱ እና ተገንብቶ ሲጠናቀቅም ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድልን የሚፈጥርና ዞኑን ከቱሪዝም ገቢ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ትናንት የደንቢ ሀይቅ ሎጅ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ተከትሎ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች በፕሮጀክቱ ጅማሮ መደሰታቸውን ገልጸዋል።


 

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ያሬድ ካንጃ ''ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት መጀመሩና በቦታው መገኘታቸው ለአካባቢያችን ትልቅ ትርጉም ያለውና ሊበረታታ የሚገባው ነው" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ተደራሽ ያለመሆን የአካባቢውን የመልማት ሁኔታ ወደ ኋላ ማስቀረቱን ጠቅሰው ከለውጡ በኋላ መንግስት በአካል ወርዶ በማየት ተስፋ ሰጪ ተጨባጭ ልማቶችን እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ከደንቢ ሀይቅ የሎጅ ፕሮጀክት ቀድሞ አካባቢው ከማዕከል ያለውን ርቀትና ያለውን እምቅ የግብርና ምርቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እነዚህ በአካባቢያችን የታዩ ጅምር ሥራዎች አሁን ላይ እንደ ሀገር የልማት ፕሮጀክቶች በምክንያት እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ታይተው እየተሰሩ እንዳለ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ማርታ ጋይንሰብ የደንቢ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራ ቢሆንም ታይቶ ሳይለማ እና አገልግሎት ሳይሰጥ ለብዙ ዘመናት የቆየ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንደ ሀገር ባሉን የተፈጥሮ ሀብቶች መልማትን መሠረት ባደረገ ፕሮጀክት ይህ ሀይቅ ፈጥኖ ወደ ልማት እንዲገባ ማድረጋቸው ትልቅ አንድምታ እንዳለው ገልጸዋል።

ከምንም በላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦታው መገኘት የአካባቢውን እውነተኛ ማንነት በማስተዋወቅ ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባው ጠቅሰዋል።

በአካባቢያችን ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለማልማት መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ አካባቢውን ለማሳደግ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ኤልያስ ሽባብ ናቸው።


 

መልማት የሚገባቸውን አካባቢዎች መንግስት በአግባቡ አይቶ ደረጃ በደረጃ እየሰራ እንዳለ ትናንት በተቀመጠው የደንቢ ሀይቅ ሎጅ አረጋግጠናል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ እና የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ መንግስት የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት አስደሳች ነው ብለዋል።

የደንቢ ሀይቅ ሎጅ በግንባታው ሂደትና እና ተሰርቶ ሲጠናቀቅም ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድልን የሚፈጥርና የቱሪዝም ፍሰትን ለዞኑ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።

የዞኑ አስተዳደር ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ በቅርበት የመከታተልና የመደገፍ ሥራን  በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።


 

የደንቢ ሰው ሰራሽ ሀይቅ የእምቅ ደን፣ የፏፏቴ እና የብርቅዬ አዕዋፋት መኖሪያ የሆነ አረንጓዴ የመስህብ ሥፍራ ነው።

መንግስት በ''ገበታ ለትውልድ'' ስምንት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንደሚያለማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽ በሰጡበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም