ቀጥታ፡

ኮርፖሬሽኑ በ100 ሚሊዮን ብር ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በአዳማ አስጀመረ

አዳማ መስከረም 21/2016(ኢዜአ) :-የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ100 ሚሊዮን ብር የቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በአዳማ አስጀመረ።

የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረተ ድንጋይ በኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እና በአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ዛሬ ተቀምጧል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ኮርፖሬሽኑ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች በስፋት እየተሳተፈ ነው።


 

በተለይም የትምህርት ቤቶች ደረጃን በማሻሻል ረገድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያረጁ የመማሪያ ክፍሎች እድሳት፣ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ግንባታ ላይ እየተሳተፈ መሆኑን አመልክተዋል።

በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ በ100 ሚሊዮን ብር አንድ የቡዑራ ቦሩ (ቅድመ መደበኛ) ትምህርት ቤትን ጨምሮ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ አስጀምረናል ብለዋል።

የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታውን በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ አጠናቀው በመጪው ዓመት ተማሪዎችን ተቀብለው እንዲያስተምሩ ለማስቻል ነው ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ትውልድ ከጅምሩ አንስቶ በስነ ምግባርና በሰብዕና የሚገነባበት ትምህርት ቤቶችን ገንብተው በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አካባቢ ለሚገኙና መሬታቸውን ለኢንዱስትሪው ልማት ለለቀቁ የማህበረሰብ ክፍል ልጆች በቄያቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው ብለዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው አስተዳደሩ ትውልዱን በዕውቀት፣ በስነ ምግባርና ግብረገብነት ለማነፅ  ህብረተሰቡን፣ ባለሃብቶችና የልማት ድርጅቶችን ጭምር በማስተባበር በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም በርካታ የቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ጭምር መገንባታቸውን ገልጸዋል።

ለኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታው እንዲሆን አስተዳደሩ 300 ሄክታር መሬት በመስጠትና የአካባቢው ህብረተሰብ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ደህንነት እንዲጠብቅና ለልማቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ማስቻሉንም ከንቲባው አክለዋል ።

ኮርፖሬሽኑ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጡ ፓርኩ የአካባቢውን ህብረተሰብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ለመሆኑም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብ የፓርኩን ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ  እያደረገ ያለውን እገዛ አሁንም አጠናክሮ በማስቀጠል የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ፈጥነው እንዲጠናቀቁ የተለመደውን ትብብሩን እንዲያጠናክር አስገንዝበዋል።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ1ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ ናቸው።

በተጨማሪም የትምህርት ቤቶች ደረጃን ለማሻሻል የተጀመረውን ንቅናቄ ለማገዝ በቡርቃ ቦኩና በዳቤ ቆጬ የመማሪያ ክፍሎች እድሳትና ጥገና ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ዛሬ የትምህርት ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ጠቅሰው ፓርኩ ግንባታቸው በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም