ቀጥታ፡

ኢዜአ በሀገሪቱ  የሙስና መከላከል ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የመረጃና የግንዛቤ ስራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል- አቶ ተፈራ በቀለ  

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገሪቱ  የሙስና መከላከል ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የመረጃና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አጠናክሮ  እንደሚቀጥል የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ ገለጹ።

ለዚህም የተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ስልጠናዎችን በመስጠት ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ እንዲደርስ የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ኢዜአ ከፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለኮሚሽኑና ለክልል የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል።

ስልጠናው ባለሙያዎቹ የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀማቸውን ማጎልበት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተፈራ በቀለ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አገልግሎቱ በተሰጠው አገራዊ ኃላፊነት መሰረት ዜናና ዜና ነክ የሆኑ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

በተጨማሪም የተለያዩ ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በዘርፉ ላይ ያላቸውን አቅም ለማሳደግ ኢዜአ በርካታ ስራዎችን እያከነወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገሪቱ  የሙስና መከላከል ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የመረጃና የግንዛቤ ስራዎችን አጠናክሮ  እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ለስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና ባለሙያዎቹ እንደ ሀገር የሙስና መከላከል ስራዎችን የማጠናከር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የፌደራል ስነ ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ኮከብ አንበርብር በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድና ዜጎች በመልካም ስነ ምግባር እንዲታነጹ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኢዜአ ጋር በመተባበር የሚሰጠው ስልጠና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በአገር ደረጃ ሙስናን ለመከላከል የሚከናወኑ ስራዎችን ተደራሽ የማድረግ አቅማቸውን ለማጎልበት ያለመ እንደሆነም ጠቁመዋል። 

ባለሙያዎቹ በስልጠናው የሚያገኙትን ክህሎት በመጠቀም እንደ አገር የተጀመረውን የፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችላቸውን ስራ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።

ስልጠናው ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም