የገበታ ለሀገር እሳቤ የኢትዮጵያን እምቅ ፀጋ በመለየት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የመትጋት ሁነኛ ማሳያ ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የገበታ ለሀገር እሳቤ የኢትዮጵያን እምቅ ፀጋ በመለየት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የመትጋት ሁነኛ ማሳያ ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2016 (ኢዜአ)፦ የገበታ ለሀገር እሳቤ የኢትዮጵያን እምቅ ፀጋ በመለየት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የመትጋት ሁነኛ ማሳያ እንደሆነ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገለፁ።
በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ቡድን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችና የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ከጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ እስከ ሀላላ ኬላ፣ ከኮይሻ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ እስከ ዳውሮ ህዝብ ኢትኖግራፊ ቤተ መዘከር ተዘዋውረው ቃኝተዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የሚዲያ ባለሙያዎች ጉብኝት ዓላማ በሚገባው ልክ ያልተነገረውን የአካባቢውን የቱሪዝም አቅም የማስተዋወቅ ያለመ ነው ብለዋል።
በጉብኝቱም ከቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ባሻገር የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ሜጋ ፕሮጀክትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች ቅኝት መደረጉን ገልፀዋል።
የኮይሻ ሜጋ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም ከተያዘለት እቅድ መጓተቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ መንግስት በወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች በፈጣን አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በጉብኝቱ በርካታ የእንስሳት እና የዕፅዋት ብዝኃ ሕይወት የሚገኙበት የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ገና ያልተነካ ዕምቅ አቅም እንዳለው ግንዛቤ መያዙን ገልፀዋል።
መንግስት ይህን ፀጋ የማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ ምጣኔ ሀብታዊ አበርክቶ የመለወጥ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የሐላላ ኬላ ታሪካዊ ቅርስን ጨምሮ ከሥነ ምህዳር ጋር በተጣጣመና እሴቱን በጠበቀ መልኩ የተደረጉ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች በአነስተኛ ወጪ ውጤታማ ስራን ማከናወን እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
የገበታ ለሀገር እሳቤ ኢትዮጵያ ያሏትን ዕምቅ ፀጋዎች ወደ በረከት በመለወጥ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንዲውሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲነሳሱ ያደረገ ሀሳብ እንደሆነ አንስተዋል።
መንግስት ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረው፤ ይህን አጋጣሚ የግል አልሚዎችም ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በሌሎች ክልሎችም ሰፊ እምቅ የመልማት አቅም እንዳለ ጠቅሰው፣ በቀጣይ የሚተገበረው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክትም ዛሬና ነገን የሚያስተሳስር ነው ብለዋል።
ሚዲያዎችም ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ጸጋ በማወቅ የሀገርን ገፅታ ለመለወጥና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ማስተዋወቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የመንገድና የኃይል አቅርቦት መሰረተ ልማትን ተደራሽ የማድረግ፣ የመንግስት አሰራርን የሚያቀላጥፉ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም ነው ያነሱት።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ብላቴ በበኩላቸው፤ ክልሉ ከተዋቀረ አጭር ጊዜ ቢሆንም በሁሉም ዞኖች ያሉ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የመስህብ ስፍራዎችን የማስተዋወቅና የማልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
እነዚህ ዕምቅ አቅሞችን ከማልማትና ወደ ኢኮኖሚ ከመለወጥ አኳያ ብዙ የሚጠበቅ ስራ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዳውሮና ኮንታን በመጎብኘት የኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እንዲሰራ ማድርጋቸውም ለአካባቢው ትልቅ የለውጥ መንገድ መክፈቱን ጠቅሰዋል።
ለአካባቢውና ለክልሉ አዲስ ለውጥና ገፅታ እንዲሁም ለቱሪዝም ዘርፉ እመርታ ያመጣ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ እንዲመጡ የኢንቨስትመንት ህግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለቱሪዝም ዕድገት የመስህብ ስፍራ፣ ማረፊያ ስፍራዎችና መሰረተ ልማት እንደሚሻ ጠቁመው፣ ባለሀብቶችን በማስተባበር መሰረተ ልማትን የማሟላት ስራ ትኩረት እንደሚሰጠው አረጋግጠዋል።
በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የማስተዋወቅ እና በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች መረጃ ለጎብኚዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻልም እንሰራለን ነው ያሉት።