ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) “ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ” ረቂቅ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ማካሄዱን አስታወቀ፡፡
በመድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ የመከላከያ ሚንስቴር፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የብሄራዊ ባንክ እና ሌሎችም መሰል የመንግስት ተቋማት ተሳታፊ ሆነዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ባስተላለፉት መልእክት የሳይበር ምህዳሩ የሚያሳያቸው ለውጦች ፈጣን እና ኢ-ተገማች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲው የሳይበር ምህዳሩ ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ እኩል የሚራመድ እና ለወቅቱ የሚመጥን እንዲሆን በማለም ረቂቅ ፖሊሲው መቀረጹን ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ለማዘጋጀት ገፊ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ሳይበር ድንበር ተሻጋሪ ክስተት መሆኑ እና ባህሪው ተለዋዋጭነት የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰው ሀገሪቱ እየተገበረችው ያለው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሳይበር ደህንነት በይበልጥ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑ አንስተዋል፡፡
ከአየር ንብረት ቀጥሎ ትልቁ የአለም ስጋት የሳይበር ጥቃት መሆኑንና የሳይበር ዲፕሎማሲን ማሳደግ እና የዲጂታል ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲው ወቅቱን ያማከለ ተደርጎ መቀረጹ ትልቅ መነሻ ሆኖናል ሲሉም አብራርተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ ባስተላለፉት መልዕክት የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የሁሉም አካላት ሃላፊነት መሆኑንና ይህንንም ለማረጋገጥ ዜጎች፣ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ ቀዳሚ ጉዳይ አድርጎ እየሰራ ያለው የቴክኖሎጂ እድገትንና የሳይበር ተለዋዋጭ ባህሪን ያማከለ ወቅቱን የሚመጥን የፖሊሲ ረቂቅ መዘጋጀቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላት የፖሊሲውን አስፈላጊነት ጠቅሰው ፖሊሲው ያሉበትን ክፍተቶች እና ሊይዛቸው ስለሚገቡ ነጥቦች ከተቋማቸው ፍላጎት አንፃር ሃሳቦችንና ጥያቄዎችን በማቅረብ ምላሽና ማብራሪያ መስጠቱን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡