ቀጥታ፡

የቡና ልማት እሴት ሰንሰለት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2016(ኢዜአ)፦ የቡና ልማት እሴት ሰንሰለት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ  መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።    

በአዲስ አበባ ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚካሄደውን ስብሰባ በማስመልከት "ውሜን ኢን ኮፊ ኢትዮጵያ" ማህበር እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ስብሰባ "ዓለም አቀፍ ውሜን ኢን ኮፊ ኮንቬንሽ" የሚል መጠሪያ እንደተሰጠው በመግለጫው ተመላክቷል።    

ከጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሚካሄደው ጉባኤ የዓለም አቀፍ ውሜን ኢን ኮፊ አሊያንስ /ህብረት/ አባል አገራት ይሳተፉበታል ተብሏል።      

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሀመድ ሸምሱ፤ በጉባኤው 300 የሚሆኑ የቡና ዘርፍ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ሁነቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው የአሁኑ ስብሰባም በመስኩ የሴቶች ተሳትፎ እንዲጎለብት የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ውሜን ኢን ኮፊ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ሳራ ይርጋ፤ መድረኩ የውጭ አገር ገዥዎችን በቀጥታ ለመሳብ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ በቡናው ዘርፍ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅም ምቹ አጋጣሚ ይሆናል ብለዋል።  


 

የስብሰባው ተሳተፊዎች ምርታቸውን የሚያቀርቡበት ኤክስፖ የተዘጋጀ ሲሆን በተመረጡ ቡና አምራች አካባቢዎች ጉብኝት የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ውሜን ኢን ኮፊ ማህበር ሴቶችን በማደራጀት ከቡና ልማት የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

በመስከረም 2009 ዓ.ም ስራ የጀመረው ማህበሩ እኤአ ከ2017 ጀምሮ ደግሞ የዓለም አቀፍ ውሜን ኢን ኮፊ አሊያንስ /ህብረት / አባል ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም