“ዱቡሻ” የተሰኘው የጋሞ ብሔር ባህላዊ የሸንጎ ሥርዓት ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው-የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
“ዱቡሻ” የተሰኘው የጋሞ ብሔር ባህላዊ የሸንጎ ሥርዓት ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው-የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ

አርባ ምንጭ፤ መስከረም 20/2016(ኢዜአ)፦ “ዱቡሻ” የተሰኘው የጋሞ ብሔር ባህላዊ የሸንጎ ሥርዓት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ ለማህበራዊ መረጋጋትና ሰላማዊ ህይወት ከፍተኛ ፋይዳን እንደሚያበረክት የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ ገለጹ።
“ዱቡሻ” ን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
አቶ ሞናዬ ሞሶሌ ለኢዜአ እንዳሉት “ዱቡሻ” የተሰኘው የጋሞ ብሔር ባህላዊ የሸንጎ ሥርዓት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ ለማህበራዊ መረጋጋትና ሰላማዊ ህይወት ከፍተኛ ፋይዳን የሚያበረክት ነው ፡፡
በዚህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ይህ ሥርዓት የህዝቡን ሰላም፣ አብሮነት፣ መቻቻልና አንድነቱን በማጽናት ረገድ የማይተካ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ግጭቶች እንደሚስተዋሉ የጠቀሱት አቶ ሞናዬ እንደ ዱቡሻ ያሉ የሸንጎ ሥርዓቶች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ስሉም አክለዋል፡፡
ይህን ሥርዓት ለማሳደግና ለማበልጸግ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ካሉ የባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ መፈራረማቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ሞናዬ ገለጻ በያዝነው የበጀት ዓመት በእነዚህ ተቋማት አማካይነት በ”ዱቡሻ” ሥርዓት ዙሪያ ጥናት የሚደረግ ሲሆን ለጥናቱ ማስፈጸሚያ ደግሞ 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቧል፡፡
በአካባቢው ባህላዊ እሴቶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጽሑፍ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ተመስገን ምንዋጋው “ዱቡሻ” ለሚያጋጥሙ ያለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ረገድ ሚናው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
''ዱቡሻ'' የህዝቡን ችግሮች በዘላቄታዊነት ከመፍታት ባለፈ ለፍትህ ሥርዓቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡
ባህላዊ የሸንጎ ሥርዓት የሚካሔድባቸው ስፍራዎች በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው ባህላዊ እሴቱ ለህዝቡ ከሚያመጣው ዘላቂ ሰላም አንጻር ለመጪው ትውልድ መተላለፍ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
“ዱቡሻ” በሀገራችን ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ከመምጣቱ በፊት የነበረና እስካሁን ድረስም ህዝቡ በሰላም፣ በመቻቻል፣ በመፋቀርና በመረዳዳት እንዲኖር ዘመን ተሻጋሪ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋሞ የሃገር ሽማግሌ አቶ አመሌ አልቶ ናቸው፡፡
"ዱቡሻ" ላይ የማይፈታ ማህበራዊ ችግር የለም ያሉት አቶ አመሌ አልቶ በሀቅ ላይ የተመሠረተ፣ ቂምና ቁርሾ የሌለው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡