የተፈጥሮ ጸጋዎች ላይ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን መሠረት ይጥላሉ- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ጸጋዎች ላይ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን መሠረት ይጥላሉ- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2016(ኢዜአ)፦የተፈጥሮ ጸጋዎችን ከሰው ኃይል ጋር በማስተሳሰር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በጅማ እና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በዋናነት በአካባቢዎቹ የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋት፣ እንዲሁም የግብርና ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን፤ በጅማ ከተማ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት የሚከናወነው የቱሪዝም ልማት ሥራም የጉብኝቱ አካል ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ በጉብኝታቸው በጅማ ዞን ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው በቡና፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቱሪዝም ልማት አበረታች ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ይህም የፌደራል መንግሥት ከክልሎች ጋር በመቀናጀት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ሥራዎች በውጤታማ መንገድ ላይ መሆናቸውን ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ መሰል የልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡
ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አፈ- ጉባዔው አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በርካታ ፈተናዎችን በጋራ በማለፍ አብሮነታቸውን አስጠብቀው መቀጠላቸውን አስታውሰው፤ ይህንን የሕዝብ አብሮነት በልማት ሥራዎች በማስተሳሰር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በሌማት ትሩፋትና ቱሪዝም ልማት የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አባ ዱላ ገመዳ በበኩላቸው፤ በጉብኝታቸው በጅማ ከተማና አካባቢው በርካታ አዳዲስ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ከዚህ ቀደም በአካባቢው የማይመረቱ እንደ ሩዝ ያሉ ምርቶችን በስፋት ማልማት መቻሉን ጠቅሰው፤ የቡና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ረገድም ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይ በጅማ ከተማ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ አቅም እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡
በሌማት ትሩፋትና ግብርና ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት በማሳለጥ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አኳያ አመራሩ በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በሁሉም አካባቢዎች በማስቀጠል ረገድ ይበልጥ መሥራት እንዳለበትም አቶ አባ ዱላ ገመዳ ተናግረዋል፡፡