በምዕራብ ወለጋ ዞን ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰቱ ህብተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው

ግምቢ/መስከረም 20/2016 (ኢዜአ)--  በምዕራብ ወለጋ ዞን የወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡን ባሳተፈ  መልኩ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ሰለሞን ጫላ እንደገለጹት በዞኑ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ የወባ በሽታና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡብን ባሳተፈ መልኩ ለአካባቢ ጽዳት ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

በዞኑ ዘንድሮ የወባ ወረርሽኝ በ13 ወረዳዎች መከሰቱን ተናግረው፤ በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ የመቆጣጠር ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች ለወባ ትንኝ መራቢያ ሊሆኑ የሚችሉ ሥፍራዎችንና ውሃ የሚያቁሩ ቦታዎችን የማጽዳት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሕዝብ ተሳትፎ ዘመቻ ስራው የጸጥታ አካለት ጭምር እየተሳተፉ ሲሆን አካባቢን የማጽዳት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአካባቢ ጽዳት ጎን ለጎን በዞኑ በ13 ወረዳዎች በ100 ሺህ በላይ ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

678 ሺህ  የአልጋ አጎበር ለተጠቃሚዎች አስቀድሞ እንዲደርስ ተደርጓል ያሉት  ኃላፊው ከ74 ሺህ በላይ ዜጎች በበሽታው እንዳይጠቁ ማድረግ ተችሏል ብለዋል ፡፡ 

የጤና ባለሙያዎችም ህዝቡን ከበሽታው ለመታደግ ቤት ለቤት በመሄድ የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ላይ የግንዛቤ መስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡


 

የጊምቢ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሉጬ መገርሳ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለውን የወባ በሽታ ለመከላከል የግላቸውንና የአካባቢያቸውን ንጽሕና በአግባቡ በመጠበቅ ከበሽታው ራሳቸውን እየጠበቁ እንደሆነ ነው የገልጹት፡፡

ለወባ ትንኝ መራቢያ ሊሆኑ የሚችሉና ውሃ የሚያቁሩ ስፍራዎች የመደፍን ስራ ከሌሎች ጎረቤቶታቸው ጋር እያሰሩ መሆኑን ተናገረዋል።

''የግልም ሆነ የአካባቢ ንጽሕና መጠበቅ ለራስ ነው'' ያሉት የጊምቢ ከተማ ነዋሪው አቶ ናደው አምሳሉ የግላቸውንና አካባቢያቸውን ንጽህና ከመጠበቅ ባለፈ የአልጋ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም በሽታውን እየተከላከሉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም