በዞኑ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ማህበረሰብ አቀፍ የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው- መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ማህበረሰብ አቀፍ የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው- መምሪያው

ዲላ መስከረም 19/2016 (ኢዜ)..በጌዴኦ ዞን የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ማህበረሰብ አቀፍ የመከላከል ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ።
በዞኑ የወባ በሽታ ስርጭት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭትና የተለያዩ የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም ተመላክቷል።
የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መስፍን ዱቤ ለኢዜአ እንዳሉት የወባ በሽታ ወረርሽኝ የዞኑ የጤና ስጋት ነው።
ዞኑ በተጠናቀቀው ዓመት ከወባ በሽታ ስርጭት ነጻ የሆነው ለአራት ሳምንታት ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ይህም አካባቢው ዓመቱን ሙሉ በወባ በሽታ ስርጭት ውስጥ እንደሚገኝ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የወባ በሽታ ህክምናና የምርመራ ግብዓት እጥረት፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግር እንዲሁም የአካባቢ ጽዳት የወባ በሽታ ስርጭትን ተጠቃሽ ማነቆ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በዞኑ የበሽታው ጫና ከፍተኛ በሆነባቸው ዲላና ጨለለቅቱ ከተማ እንዲሁም ዲላ ዙሪያ ወረዳ 8 ሺህ 200 አባዎራዎችን ተደራሽ ያደረገ ርጭትና የአጎበር ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም አብራርተዋል።
በተያዘው የክረምት ወራት ስርጭቱን ለመግታት የሚያስችሉ ማህበረሰብ አቀፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አስተባባሪው ገልፀዋል።
የዲላ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ በየነ በበኩላቸው በከተማው በተለያዩ ቦታዎች ላይ የፀረ ወባ ኬሚካል እርጭትን ጨምሮ የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በዚህም በከተማው በበሽታው አማካይነት የሚከሰት የሞት አደጋን ማስቀረት ከማስቻል ባለፈ የበሽታውን ጫና መመከት መቻሉን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ የፀረ ወባ መከላከያ አማራጮችን በመጠቀም እራሱን ብሎም አካባቢውን ከወባ በሽታ እንዲከላከልም ጥሪ አቅርበዋል።
የዲላ ከተማ በዞኑ ካሉ ከተሞች የወባ በሽታ ጫና ያለበት በመሆኑ በክልል ደረጃ በሽታውን ለማጥፋት ልዩ ትኩረትን ካገኙት አንዱ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የዲላ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት የወባ መከላከል ተጠሪ አቶ ጳውሎስ ወልደጊዮርጊስ ናቸው።
በተለይ ለወባ ትንኝ መራቢያ የሚሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ከማስወገድ ባለፈ 54 ሺህ 139 አጎበሮች ስርጭት እንዲሁም ምልክት በታየባቸው አካባቢዎች የቤት ለቤት ምርመራና የመድሃኒት እደላ እየተከናወነ እንደሆነም ገልፀዋል።
የፀረ-ወባ ኬሚካሉ ወባ ትንኝን እንዳትራባ ከማድረጉም በላይ ጠረን የሌለውና የቤት ቀለም የማያበላሽ በመሆኑ ቤታቸውን ማስረጨታቸውን የተናገሩት ሃሮሬሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደሳለኝ ገልፈቶ ናቸው።
በቀበሌያቸው በበሽታው የተጠቃ ሰው ሲገኝ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም እንዲሄድና በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችን ደግሞ በቶሎ ምርመራ እንዲያደርጉ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጌዴኦ ዞን ከወባ በሽታ ስርጭት ነፃ ከሆነባቸው አራት ሳምንታት ውጪ አመቱን ሙሉ በሳምንት እስከ 120 አዲስ የወባ በሽታ ኬዝ እንደሚመዘገብ ከዞኑ ጤና መምሪያ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።