የቱሪዝም ዘርፉን የሀገር ኢኮኖሚ ልማት መሠረት ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው- የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2016 (ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ የሀገር ኢኮኖሚ ልማት መሠረት ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ቱሪዝም የሀገር በቀል ዕውቀትን በማበረታታት ለአዲሱ ሥርዓተ-ገቢራዊነት ገንቢ ሚና እንደሚወጣም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገልጿል።

በዓለም ለ44ኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ "ቱሪዝምና አረንጓዴ ኢንቨስትመንት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረው የቱሪዝም ቀን በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከናወነ ነው።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከስልጤ ዞን ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መርሃ-ግብር ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የክልሉና የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ፤ የቱሪዝም ዘርፍ የሀገር ኢኮኖሚ ልማት መሠረት ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

በመንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ እድገትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተለያዩ ተግባራት መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ካለው ሃብት አንፃር ተጠቃሚ ለመሆን በቀጣይ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
​​​​​​​

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ፤ ኢትዮጵያ በርካታ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ኃብቶች መስህብ ባለቤት ብትሆንም ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ውስንነቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ግን የቱሪስት መዳረሻዎች በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው ተካተው የሀገር ሀብትና ኢኮኖሚውን የሚደግፉና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መስክ በማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ ከድር፤ በዞኑ በርካታ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ሥፍራዎችና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻዎች ቢኖሩም እስካሁን እምብዛም ጥቅም አልተገኘባቸውም ብለዋል።

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ እየተነቃቃና በርካታ ጥቅሞች እየተገኙበት ነው ብለዋል።

በዞኑ ያሉ ሙጎ ተራራ፣ የአባያ ጡፋ ሀይቅ፣ የሀጅ አሊዬ መስጂድ እና ሌሎችም የቱሪስት መዳረሻዎችን በመለየት ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም