በምዕራብ ጎንደር ዞን ምርታማነትን ለማሳደግ  የተባይ መከላከልና የአረም ስራ እያከናወን ነው- አርሶ አደሮች 

መተማ ፤ መስከረም 20/2016 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን የመኸር ሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የተጠናከረ የተባይ መከላከልና የአረም ስራ እያከናወኑ መሆኑን የዞኑ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በዞኑ በመኸር ወቅት ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብሎች  መልማቱም ተገልጿል።

የመኸር ሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ታዲያ አርሶ አደሮቹ በባለሙያ በመታገዝ የተጠናከረ የተባይ መከላከልና የአረም ስራ እያከናወኑ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዞኑ መተማ ወረዳ የገንዳ ውሃ ብርሽኝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሀሰን ሙሃመድ እንዳሉት፤ በዚህ የመኽር ወቅት 10 ሄክታር ማሳቸውን በተለያዩ ሰብሎች ሸፍነዋል።

ማሽላና በቆሎን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን ማልማት መቻላቸውን ጠቅሰው፤ የሰውን ጉልበት በመጠቀም የአረም ስራ ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

በ4 ሄክታር መሬት ማሽላና በቆሎ ሰብል ተከስቶ የነበረውን ተባይም ባደረጉት የመከላከል ስራ ምንም ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻላቸውን ገልፀዋል።

አሁን ላይ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ እና ካለሙት ሰብልም ከ170 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ሌላኛው በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የጠረፍ ወርቅ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ባየ መለሰ በበኩላቸው፤ በመኸር ወቅቱ በ20 ሄክታር መሬት ያለሙትን ሰብል የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራ ወቅቱን ጠብቀው እያከናወኑ ነው።

በአካባቢው አጠራር ''መጣጭ'' ተብሎ የሚጠራው ተባይ በሰሊጥ ሰብል ተከስቶ የነበረ ቢሆንም ወዲያውኑ ባከናወኑት መከላከል መቆጣጠር እንደቻሉም ገልፀዋል።

እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ የአረም ስራውን የሰው ጉልበት በመጠቀም ሦስት ጊዜ ያህል ማረም የቻሉ ሲሆን በባለሙያ እገዛ  ኬሚካል በመርጨትም ተባዩን መከላከል እንደቻሉ ተናግረዋል።

ባደረጉት የጠናከረ የተባይ መከላከልና የአረም ስራም ካለሙት መሬት 250 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸው፣ መሰል እንክብካቤ ምርታማነት እንደሚጨምር ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጌትነት ካሳሁን እንዳሉት፤ በዚህ የምርት ዘመን በዞኑ ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ማልማት ተችሏል።

የለማው ሰብልም ካለፈው የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር 50 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ብልጫ ያለው መሬት መሆኑን ተናግረዋል።

የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራ ወቅቱን ጠብቆ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው፤ አሁን ባለው የሰብል ቁመና በቅድመ ምርት ግምገማ መሰረት የተሻለ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም