የክልሉን ፖሊስ በግብዓት፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የማጠናከር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ኦርዲን በድሪ

ሐረር መስከረም 20/2016 (ኢዜአ) ... የክልሉን ፖሊስ  በግብዓት፣በክህሎትና በቴክኖሎጂ የማጠናከር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል  ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በክልሉ በቅርቡ ከተመረቁ የፖሊስ አባላት ጋር የትውውቅ እና የስራ መመርያ በሰጡበት ወቅት ነው።

የፖሊስ ተግባር ከራስ በፊት ለህዝብ ቅድሚያ መስጠት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የፖሊስ አባላቱ   የዜጎችን ደህንነት መጠበቅና የህግ የበላይነትን በማስፈን  ለህዝብ ቅን አገልጋይ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የፖሊስ ተቋማት ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት ካልሰሩ ወንጀልን የመከላከል ተልዕኮ ውጤታማ እንደማይሆን ጠቅሰው፤ ለዚህም ሁሌም ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው አመልክተዋል። 

ዜጎች በየትኛውም ጊዜና አካባቢ በነጻነት ተንቀሳቅሰው በአገር ልማት ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ከማንኛውም ጥቃት በመጠበቅ ሰላምና ጸጥታ ለማስፈን በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ  ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ባከናወነው የሪፎርም ስራ በክልሉ አበረታች የሰላምና የጸጥታ ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ተቋሙን በግብዓት፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የማጠናከር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል  ሲሉ አረጋግጠዋል።


 

ከኮሚሽኑ ተቋማዊ ሪፎርም ወዲህ "ቀድሞ ይታዩ የነበሩ ችግሮች መቅረፍ ተችሏል" ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘከርያ ናቸው።

በዚህ ፖሊስ ከማህበረሰቡ  ጋር በመቀናጀት በሚያከናውነው የሰላምና ጸጥታ ስራ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛልም ብለዋል።

ዘንድሮ የተመረቁ ፖሊሶችም የክልሉንና የአካባቢውን ሰላም እና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ የሚከናወነውን ተግባራት ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ  ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን  መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ. ም  491 የፖሊስ አባላትን አሰልጥኖ  ማስመረቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም