በስልጤ ዞን የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን በመለየት ለጎብኝዎች ምቹ ተደርገዋል- የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
በስልጤ ዞን የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን በመለየት ለጎብኝዎች ምቹ ተደርገዋል- የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2016 (ኢዜአ)፦ በስልጤ ዞን የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን በመለየት ለጎብኝዎች ምቹ መደረጋቸውን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ገለጹ።
የዓለምን የቱሪዝም ቀን በማስመልከት "ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት፣ አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም" በሚል መሪ ሃሳብ የስልጤ ዞን የቱሪስት መዳረሻዎች ሲምፖዚየምና ጉብኝት እየተካሄደ ነው።
የስልጤ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ይርዳው ናስር፤ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን በመለየት ለጎብኝዎች ምቹ መደረጋቸውን ገልፀዋል።
የተለያዩ ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ቅርሶችና ሌሎችም የቱሪስት መስህቦችን ከቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር መለየታቸውን ተናግረዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አሊ ከድር በበኩላቸው፤ በዞኑ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በመለየት ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግ ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል።
ለጉብኝት የሚመጡ ሁሉ የአካባቢውን ባህላዊ ምግቦች በልዩ ሁኔታ በማቅረብ የሚስተናገዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የስልጤ ባህላዊ ምግቦች በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ ተካተው ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ የማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ፤ የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች እና ባህላዊ ምግቦች በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ ተካተው ለዓለም በስፋት መተዋወቅ አለባቸው ብለዋል።
ለዚህም በመላ ሀገሪቱ ያሉ ሀብቶች በጥናት ተለይተው እንዲሰነዱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ከቱሪዝም ዘርፍ እስካሁን እየተገኘው ያለው ጥቅም አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በቀጣይ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከተጠቃሚነት አንፃር ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።