የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስጀመራቸውን 203 ቤቶች ለነዋሪዎች አስረከበ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2016(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስጀመራቸውን 203 ቤቶች ለነዋሪዎች ዛሬ አስረክቧል።

ርክክቡን አስመልክቶ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት በክረምት ወራት የተጀመሩ የአቅመደካሞችንና የሃገር ባለውለታዎችን ቤቶች የመገንባት ስራ በማጠናቀቅ ዛሬ ለ203 ነዋሪዎች ማስረከብ ተችሏል።


 

ዛሬ ያስተላለፍናቸውን ጨምሮ ልበ ቀና ባለሃብቶችን፣ የግል እና መንግስታዊ ተቋማትን እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞችን በማስተባበር ያስገነባናቸውን በጠቅላላ 1889 ቤቶች ከአዲስ ዓመት ወዲህ ለነዋሪዎች አስተላልፈናል ሲሉም ገልጸዋል።

ከንቲባዋ አያይዘውም በዚህ በጎ ስራ ላይ አሻራችሁን ያኖራችሁ አመራሮችን፣ ልበቀና ባለሃብቶችን ፣ የመንግስትና የግል ተቋሞችን እንዲሁም ሰራተኞችን በነዋሪዎቹ ስም ላመሰግን እወዳለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም