በላቲቪያ ሪጋ በሚካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ13 አትሌቶች ተወከላለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- በላቲቪያ ሪጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ በሚደረገው የዓለም ጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው 13 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

በሻምፒዮናው ከ57 አገራት የተወጣጡ 347 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን 1 ማይል፣ 5 ኪሎ ሜትር እና የግማሽ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ውድድር የሚካሄድባቸው ርቀቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው  በ7 ሴቶች እና በ6 ወንዶች በድምሩ በ13 አትሌቶች ትወከላለች።

በሴቶች 5 ኪሎ ሜትር እጅጋየሁ ታዬ እና መዲና ኢሳ ከቀኑ 5 ሰዓት ከ50 ላይ ውድድራቸውን ያደርጋሉ።

ከቀኑ 6 ሰዓት ከ15 ላይ በሚካሄደው ወንዶች ውድድር ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሐጐስ ገብረ ሕይወት ይወዳደራሉ።

ድርቤ ወልተጂና ፍሬወይኒ ኃይሉ 7 ሰዓት ላይ በሚካሄደው የአንድ ማይል እንዲሁም በወንዶች በተመሳሳይ ርቀት ከቀኑ 7 ሰዓት ከ10 ሰዓት ላይ በሚደረገው ውድድር ታደሰ ለሚ ይወዳደራል።

በሴቶች የግማሽ ማራቶን ውድድር ከቀኑ 7 ሰዓት 30 ጽጌ ገብረሰላማ፣ ያለምጌጥ ያረጋል እና ፍታው ዘርዬ ይሳተፋሉ።

ከቀኑ 8 ሰዓት ከ15 በግማሽ ማራቶን ወንዶች ጀማል ይመር፣ ንብረት መላክና ፀጋዬ ኪዳኑ የሚወዳደሩ ይሆናል።

ለሻምፒዮናው ውድድር አትሌቶቹ ለሶስት ሳምንታት ዝግጅት ማድረጋቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም