ባህር ዳር ከተማ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2016 (ኢዜአ)፦ ባህር ዳር ከተማ በ2023/24 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር ያካሄዳል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ 60 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሃማዲ አግሬቢ የኦሊምፒክ ስታዲየም ይከናወናል።

ክለቦቹ መስከረም 6/2016 በአበበ በቂላ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ በሀብታሙ ታደሰ ግቦች ባህር ዳር ከተማ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እየተሳተፈ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ ወደ ምድብ ድልድሉ መግባቱን ያረጋግጣል።

የጣና ሞገዶቹ በውድድሩ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የታንዛንያውን አዛም ክለብን በደርሶ መልስ ውጤት ማሸነፋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም