የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለዳውሮ ዞን ዕምቅ ፀጋዎች ትንሳኤ ሆኗል-የዞኑ አስተዳዳሪ ደስታ ደምሴ

አዲስ አበባ፤መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፦የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለዳውሮ ዞን ዕምቅ ፀጋዎች ትንሳኤ ሆኗል ሲሉ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ደምሴ ገለጹ።

በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪት የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተለያዩ የልማት ስራዎችንና ቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን እየጎበኙ ነው።

በዛሬው ዕለትም በዳውሮ ዞን ዋና ከተማ ታርጫ የሚገኘው የዳውሮ ኢቲኖግራፊ ቤተ መዘከር ተጎብኝቷል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ደምሴ እንዳሉት በአዲሱ የክልል አወቃቅር የክልሉ የማህበራዊ ክላስተር ቢሮዎች እና የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ የሆነችው ዳውሮ በአያሌ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻዎች የታደለች ናት።

ዞኑ ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው የተፈጥሮ ፀጋዎችን የታደለ ከመሆኑም ባለፈ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ሰፊ ዕድል ቢኖረውም የረጅም ጊዜ የልማትና ፍትሀዊነት ጥያቄዎቹ ሳይመለሱ ፀጋዎቹም ሳይለሙ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ከለውጡ ወዲህ ግን የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ጨምሮ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም በመንግስት ደረጃ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለቱሪዝም ለማዋል የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።


በኮይሻ
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የለማውን የሐላላ ኬላ እንዲሁም የፕሮጀከቱ አካል የሆነውን ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ታሪካዊ የሆነው የሀላላ ኬላ ቅርስ በገበታ ለሀገር እሴት ተጨምሮበት በመልማቱ የዳውሮን ገፅታ የለወጠ፣ ቱሪስቶችን ያጎረፈ እና ለአካባቢው አዲስ መልክ በመፍጠር ትንሳኤ ያመጣ መሆኑንም ገልፀዋል።

በሌላ በኩልም የዳውሮ ኢትኖግራፊ ቤተ መዘክር ሌላው የቱሪስት መስህብ ስፍራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ገበታ ለሀገርን ጨምሮ በአካባቢው እየተደረጉ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እንዲበራከቱ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ባለሀብቶች ያለውን ፀጋ እሴት ጨምረው እንዲያለሙ ጥረት እንደሚደረግ የገለጹት አስተዳደሪው፣ በተለይም ወደ ሐላላ ኬላ የሚመጡ እንግዶች ብዛት ተጨማሪ የማረፊያ ቦታ በማስፈለጉ ፈቃድ መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

በግልገል ጊቤ ሶስት ሰው ሰራሽ ሐይቅ ላይ በአሳ ሀብትና በዞኑ እምቅ የማዕድንና የግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።


ያም
ሆኖ ግን የመንገድ እና የመብራት መሰረተ ልማት ችግር ዞኑ ፀጋዎቹን የበለጠ እንዳያለማ እና ዕድሎችን እንዳይጠቀም የራሱን አሉታዊ ጫና ማሳረፉን አልሸሸጉም።

አስተዳደሩ ለኢንቨስተሮች ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረግ እና ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።

የዳውሮ ኤትኖግራፊክ ቤተ መዘክር ኃላፊ አቶ ላቀው በተላ በበኩላቸው 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የተከፈተው ሙዚየሙ የዳውሮን ህዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ የኑሮ ዘይቤ እና ጥበብ የሚዋጁ 4 ሺህ 500 በላይ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን አቅፏል ብለዋል።

ሙዚየሙ የዳውሮ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ወግ ለትውልድ የሚያስተላልፍበት መሆኑን ገልፀው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ወደ ዲጂታል ስርዓት እንዲለወጥ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ለማከናወን ጥናት መደረጉንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም