በደብረ ብርሃን ከተማ  ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች  ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ  የሚገመት የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

93

ደብረ ብርሀን ፤ መስከረም 19/ 2016 (ኢዜአ) ፡- በደብረ ብርሃን ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ  "ስንቅ " በተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት አስተባባሪነት ውጭ  ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን  የተሰበሰበ መሆኑን የድርጅቱ  ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍሰሐ ታረቀኝ ገልጸዋል።

ድጋፉ  በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ችግር ለማቃለል እንደሚያግዝ  አስረድተዋል።

ከቀረበው ድጋፍ ውስጥም 120 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 900 ሊትር የሚጠጋ የምግብ ዘይትና  ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

በተደረገው ድጋፍም 5 ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃይ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ከአምስተርዳም የኢትዮጵያዊያን ተወካይ ወጣት ናርዶስ አበበ በበኩሏ፤ በውጭ  የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ድጋፉ የሚቀጥል ይሆናል ብላለች።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሩቂያ አህመድ በሰጡት አስተያየት፤  በተለይ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ   ድጋፍ የነበረባቸውን ችግር እንዳቃለላቸው  ጠቅሰው፤  አሁንም ድጋፍ እንደሚያሻቸው አመልክተዋል።

ባለፉት ጊዜያት ማህበረሰቡ፣ መንግስትና ድርጅቶች ሲያደርጉት በነበረው ድጋፍ ያለችግር መቆየታቸውን የገለፁት አቶ ጌታቸው በላይ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ  የሚመለከተው አካል ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ  ጠይቀዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም