የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ተወያዩ

መስከረም 19/2016(ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ከተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ክልሉ የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች ተቻችለው፣ ተከባብረው እና ተዋድደው የሚኖሩበት የመቻቻል ተምሳሌት የሆነ ክልል መሆኑን አቶ አረጋ በምክክሩ ወቅት አንስተዋል።


 

በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምሮ ሰላም፣ ፍቅር፣ መቻቻል እና አብሮነት ዋነኛ መርሆዎች ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ይህንን መልካም ተግባር የሃይማኖቱ መሪዎቻ እና ታላላቅ አባቶች በየጊዜው ተከታዮቻቸውን ያለመታከት እንደሚያስተምሩ ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል ዜጎች ያለገደብ በሰላም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ነግደው እንዲያተርፉ፣ ገበያው መረጋጋት እንዲችል፣ ሕሙማን ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድ እንዲችሉ እና መድሃኒት እንዲያገኙ፣ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃቸውን አግኝተው እና አምርተው እንዲያከፋፍሉ፣ አርሶ አደሩ ምርቱን ያለምንም እንቅፋት አምርቶ ገበያ ባለበት ምርቱን እንዲሸጥ እና ያሰበውን እንዲያሳካ ሰላም ከሁሉም በላይ ትልቅ ዋጋ የሚከፈልበት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድሩ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በውይይቱ የታደሙ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች በበኩላቸው፣ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን እና የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዳይገታ የሰላም እና የፀጥታ መስፈን ወሳኝ በመሆኑ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ እና ለተከታዮቻቸው በማስተማር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የሃይማኖት መሪዎች እና ተከታዮቻቸው ለሰላም መስፈን ድርሻቸው እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የድርሻቸውን እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳድሩ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም